ጥሩ ደራሲ እንደደረሰው ቲያትር ያጓጓው ጨዋታ

0
48

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፈረንሳይ ዋና ከተማ በፓሪስ ፓርክ ዴ ፕሪንስ ስታዲየም የተካሄደው የምሽቱ ጨዋታ እንደ ልብ አንጠልጣይ ቲያትር ልብን ከፍ ዝቅ ሲያደርግ አምሽቷል። የእግር ኳስ ከዋክብት ትንቅንቅ እግር ኳስን የተለየ መልክ ሰጠው።

የአልሸነፍም ባይነት እልህ ለእግር ኳስ ውበትን ደርቦለት ታዬ። ዓለም በእግር ኳስ ጠበብት ተደመመ። በእግር ኳስ ሊቃውንት ተደነቀ።
ያ ጨዋታ እግር ኳስ አይመስልም ነበር። የሥነ ጽሑፍ፣ የታሪክ፣ የኪነ ጥበብ እና የሚቲዮሎጂ ጥልቅ ዕውቀት ያላቸው ሊቃውንት የደረሱት፣ በከፍተኛ ዝግጅት ለተመልካች ያቀረቡት ቲያትር ይመስላል እንጂ። የተመረጡ ተዋንያን የተወኑበት ልብ አንጠልጥል ቲያትር።

በፓርክ ዴ ፕሪንስ ስታዲየም ከአፍ እስከ ገደፍ የመሉትን ተመልካቶች ብቻ ሳይኾን በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የእግር ኳስ አፍቃሪያን ቁጭ ብድግ ሲያደርግ አመሸ። እግር ኳስ በፈረንሳይ ተሞሽራ አመሸች።

ትናንት ምሽት በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ፒኤስጂን እና ባየርን ሙኒክን ያገናኘው ጨዋታ የማይረሳ ኾኖ አለፈ። ብዙዎች ይህስ የሚያስደንቅ እና ያልተለመደ ነው አሉት።

ኢኤስፒኤን የትናንቱን ጨዋታ ሲገልጽ ትንፋሽ ውሰድ፣ ጭንቅላትህን አወዛውዝ፤ ከዚያም ሳቅ እና የሁለተኛው ዙር ጨዋታ መቼ እንደሚደረግ ቀኑን መቁጠር ጀምር፤ ምክንያቱም ሁለቱ የአውሮፓ ምርጥ ክለቦች እስካሁን ካየኋቸው ጨዋታዎች የተለየውን ጨዋታ አዘጋጅተዋልና ብሏል።

አስደናቂ ኾኖ ያለፈው የምሽቱ ጨዋታ በጀርመን ሙኒክ አሊያንዝ አሬና ስታዲየም የሚካሄደውን የመልሱን ጨዋታ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል።

ቢቢሲ በዘገባው እግር ኳስ ለምን “ውብ ጨዋታ” ተብሎ እንደሚጠራ ሁላችንንም የሚያስታውስ ግጥሚያ ነው ብሎታል።

እ.አ.አ በ1959/60 በአውሮፓ ዋንጫ አይንትራክት ፍራንክፈርት ሬንጀርስን 6ለ3 ካሸነፈበት ጊዜ ወዲህ በግማሽ ፍጻሜ የተመዘገበ ከፍተኛው የጎል መጠን ነው። በብዙዎች ዘንድም ለረጅም ጊዜ ሲታወስ ይኖራል።

ይህ ጨዋታ ለፍጻሜው ጨዋታ ለመድረስ የተደረገ ውብ የእግር ኳስ ምሽት ነበር። በአስደናቂ የማጥቃት ጥራት ያላቸው ሁለቱ ክለቦች ያላቸውን ሁሉ አውጥተው በመጫወታቸው ልዩ አድርገውት ነበር ይላል ቢቢሲ።

ባየርን ሙኒክ ትንፋሽ በሚያስጥል የመጀመሪያ አጋማሽ ቀዳሚ መኾን ቢችልም፣ የወቅቱ የአውሮፓ አሸናፊው ፒኤስጂ ግን በአስደናቂ ሁኔታ ተመልሶ ውጤቱን 5ለ2 አድርጎት ነበር። በዚህ ውጤትም ለአሸናፊነት ተቃርበው ነበር የሚለው ቢቢሲ ኾኖም የጀርመኑ ኃያል ክለብ ባየርን ሙኒክ ያለውን ጥንካሬ እና ብቃት በመጠቀም የጎል ልዩነቱን ወደ አንድ ማጥበብ ችሏል ብሏል። ጨዋታውም በፒኤስጂ 5ለ4 አሸናፊነት ተጠናቀቀ።

የፒኤስጂው አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ጨዋታውን ሲገልጹ “አስገራሚ ነበር፤ በአሠልጣኝነት ዘመኔ ከመራኋቸው ጨዋታዎች ሁሉ ምርጡ እንደኾነ አስባለሁ፤ ጥሩ ፍጥነት ነበረው፣ ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት እግር ኳስ ለመጫወት እና ጥራታቸውን ለማሳየት ሞክረዋል። ጨዋታውን የተመለከተ ሁሉ የተዝናና ይመስለኛል፤ እኔም ስላሸነፍን ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።

ለ15 ዓመታት በአሠልጣኝነት ቆይቻለሁ ያሉት አሠልጣኙ ይህ ግን በጣም አስደሳች ጨዋታ ነበር። እግር ኳስ መጫወት ያለበት በዚህ መንገድ እንደኾነ ማሳየት አስፈላጊ ነው። አሠልጣኝ ሲኾኑ አራት ግብ ሲቆጠርብህ ደስ አይልም፤ ነገር ግን በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ ነው ያሉት።

ጨዋታው የጎል ናዳ የታየበት የአውሮፓ ድንቅ ፍልሚያ ነበር። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የሁለቱም ክለቦች ደጋፊዎች ያሳዩት ግዙፍ ምስላዊ ትርኢት ለምሽቱ ድምቀት መጀመሪያ ነበር ይላል ቢቢሲ።

የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ታሪካዊ ተጫዋቾች አለን ሺረር ስለጨዋታው ሲናገር ” ጨዋታው ባለው ግልጽነት እና እብደት ፈገግታዬን ማቆም አልቻልኩም። እስካሁን ካየኋቸው ምርጥ ጨዋታዎች አንዱ ነው” ብሏል።

በማንኛውም የአውሮፓ ታላላቅ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ታሪክ ሁለቱም ቡድኖች ቢያንስ አራት አራት ግብ ያስቆጠሩበት የመጀመሪያው ጨዋታ እንደኾነም ቢቢሲ ዘግቧል።

በአስደናቂ ፍልሚያዎች በታጀበው በዚህ ግጥሚያ በአውሮፓ ውስጥ እጅግ አስፈሪ የኾኑት የሁለቱ ክለቦች የአጥቂ መስመሮች ፍጥጫ ኾኖ ተጠናቅቋል ይላል ቢቢሲ።

የባየርን ሙኒኩ አሠልጣኝ ቪንሰንት ኮምፓኒ ስለ ጨዋታው ሲናገሩ “ተቸግረን ነበር፤ ነገር ግን አደገኛም ነበርን፤ በሻምፒየንስ ሊግ ከሜዳ ውጭ አምስት ጎብ ሲቆጠርብህ አብዛኛውን ጊዜ ከውድድሩ ትወጣለህ ማለት ነው፣ ነገር ግን የነበሩን አጋጣሚዎች ተስፋ እንድንቆርጥ አላደረጉንም” ብለዋል።

የትናንቱ ጨዋታ በሁለቱ ክለቦች ተከላካዮች ላይ ጥርጣሬ እንዲኖር አድርጓል፤ ምክንያቱም ብዙ ግቦች ተቆጥረዋልና ይላል ቢቢሲ። ነገር ግን ይህ ጨዋታ ከምንጊዜውም ምርጥ ጨዋታዎች መካከል አንደኛው ነው።

በሚቀጥለው ሳምንት በሙኒክ አሊያዝ አሬና ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ከወዲሁ በጉጉት እየተጠበቀ ነው። ለፍጻሜ የሚደርሰው ፒኤስጂ ወይስ ባየርን ሙኒክ ? የአሊያንዝ አሬናው ጨዋታ መልስ ይኖረዋል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here