“የገና ጨዋታ እድገት በማሳየቱ ጨዋታው ባሕላዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲከናወን ሕግ እና ደንብ ተዘጋጅቶለታ” የአማራ ክልል የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን

0
364

ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የገና ጨዋታ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጀመረ የተለያዩ መዛግብት ያስረዳሉ። በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ባለሙያ ደርበው ጥላሁንም የገና ጨዋታ አዝመራ ከተሰበሰበበት ታኅሣሥ ወር ጀምሮ እስከ ጥር ወር የሚከወን ነው ይላሉ ። አልፎ አልፎም እስከ ክረምቱ ወር መግቢያ ድረስ ጨዋታው የሚቀጥልበት አጋጣሚ እንደሚኖርም ገልጸዋል።

በጥምቀት በዓልም ወጣቶች ተሰባስበው ታቦታቱን አጅበው ወደ ቤተ መቅደሳቸው ካስገቡ በኋላ ጎራ ለይተው ለጥ ባለው ሜዳ ላይ የጠነከረችው ፀሐይ ቀዝቀዝ እስክትል ድረስ ይጫወታሉ ይላሉ።

ባሕላዊው ጨዋታ የሚካሄደው በሁለት ቡድኖች መካከል ነው፡፡ ቡድኖቹ የሚዋቀሩት ሁለት በሽምግልና ወይም በነገር አዋቂነት አልያም በሐብት መጠናቸው ስመ ጥር የኾኑ አባቶች ይመረጣሉ፡፡

በቡድን አባቶች ምርጫ የሚጫወቱት ገና አንዱ በጨዋታው ተጎድቶ ቢወጣ ወይም እንግዳ ሰው ለመግባት ቢፈልግ ለጎበዝ አለቃው ወይም ለአጫዋቾቹ ተናግሮ ሲፈቀድለት ብቻ የሚገባ ይኾናል፡፡

ዘግይተው የመጡት የገና ተጫዋቾች ደግሞ የተለየ ስም በመያዝ ትከሻ ለትከሻ በመያያዝ ከሁለቱ የቡድን አባቶች ፊት እየቀረቡ ወደ ቡድናቸው እንዲቀላቀሉ ይደርጋሉ፡፡

በአንዳንድ አካባቢ የገና ጨዋታ በሚከወንበት ጊዜ አንድ የጎበዝ አለቃ አስጀማሪ እና ጨዋታውን የሚመሩ አራት የድንበር ጠባቂዎችን ይሰይማሉ ብለዋል፡፡ ጨዋታው በመንደር ወይም በቀበሌ ሊኾን ይችላል፡፡ ባገቡ እና ባላገቡ መካከልም ሊካሄድ ይችላል፡፡

የገና መጫዎቻው ከጫፉ ቆልመም (ቀለስ) ያለ እንጨት ነው፡፡ የመጫወቻ ሩሯም /ጥንጓም/ ከቆዳ ወይም ከዛፍ ስር ተጠርባ የምትወጣ ድቡልቡል ኾና የምትዘጋጅ ናት፡፡

የጨዋታው ግብ ግብ፣ ግፊያ እና በሽምጥ እሽቅድምድም ስላለው አካላዊ ጥንካሬ እና ቅልጥፍና ያላቸው፣ ተጋፍተው ማለፍ የሚችሉ ሰዎች ይጫወቱታል፡፡ ሕጻናት፣ አረጋዊያን እና ዓቅመ ደካሞች እንዲጫወቱ አይመከርም ብለዋል ባለሙያው ፡፡

ጨዋታው የተለያየ ዓይነትም አለው። “ቁርቁዝ” እንዱ የጨዋታ ዓይነት ሲኾን ሕግን በመከተል“በሚናህ” (በቦታህ) በማለት ጥንጓን በማንከባለል ብቻ የሚጫወቱት የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡

“ሙጭ”ሌላው የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ሁለቱ ቡድኖች በመጥረግ ብቻ እንጫወት ብለው በመስማማት የሰውንም አግር ኾነ ጥንጓን በመጥረግ የሚጫወቱት ነው፡፡ “ቀልቦ መለጋት” የተሰኘው ጨዋታ ከባዱ የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ሩሯን አፍሶ የመለጋት ጨዋታ ነው ብለዋል ባለሙያው።

የገና መለያ የተጫዋቾች አለባበስ ጉልበት ላይ የሚቀር ሱሪ፣ እጀ ጠባብ፣ ባተ ሁለት እና ከወገብ ላይ የሚጠመጠም “ድግ” ለብሰው ይጫወታሉ ብለዋል ባለሙያው፡፡

የገና ጨዋታ የሁሉም ጨዋታ መኾኑን ለመግለጽ “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” እየተባለ ይከናዎናል። በተጫዋቹ ላይ አደጋ ቢደርስ ቂም መያዝ እና ለበቀል መነሳሳት አይታሰብም፤ አይሞከርምም።

ለመኾኑ “በገና ጨዋታ የለም ሎሌ ጌታ፤ በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ” አንድምታው ምን ይኾን? በተፎካካሪ ቡድኖች መካከል ከሐሳብ አንስቶ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ትችት እና ነቀፌታ ይዘንባል። አንዳንዴም እስከ ስድብ ይደርሳል። መነቃቀፉ ጨዋታው የነጻነት መገለጫ መኾኑን የሚያመላክት ነው። ማንም ማንንም ከመንቀፍ የሚያግደው ወይም የሚያስፈራው ነገር አይኖርም።

በዚህ ወቅት ስጋት የኾነባቸውን ተወዳዳሪ ለማኮሰስ፣ የሠራውንም፣ ያልሠራውንም እየዘረዘሩ ድክመቱን እንደ ተራራ አግዝፈው ሊያሳዩ ይጥራሉ። በጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች በቃላት አማካኝነት ይበሻሸቃሉ፡፡ በገና ጨዋታ ወቅት የተሰደበው የባላባት ወይም የፊት አውራሪ ልጅ ቢኾን እንኳ ቂም አይዝም። ተሳዳቢውም ያሻውን ተናግሮ ይሄዳል። ሆድ ያባውም፣ ነገር ያቄመውም እንዲሁ ያሻውን ይናገራል፡፡ በመጨረሻም ሁሉም ተሳስሞ፣ አብሮ በልቶ እና ጠጥቶ ይለያያል።

ባላባቶች እና የጦር መሪዎች ጠብ መንጃቸውን አውርደው ይጫወቱ እንደ ነበር ባለሙያው አስታውሰዋል፤ እነዚህ የተከበሩ ሰዎች በጨዋታው ቢሰደቡ ወይም ቢፈነከቱ ቂም ቁርሾ አይዙም፤ለበቀል ሴራ መጎንጎን ብሎ ነገር በፍጹም አይታሰብም ብለዋል፡፡

“እናም” አሉ የባሕል እሴቶች ባለሙያው “በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ! ” ይህ ትውልድ መቻቻልን እና ትዕግስትን አጥብቆ ሊማርበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

መምህር ጌቴ ተረፈ የተባሉ የቻግኒ ከተማ ነዋሪ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳድር የሚደረገው የገና ጨዋታ መቻቻል የነገሰበት ነው ባይ ናቸው፡፡በጨዋታው አደጋ ቢፈጠር ቂም አይያዝምና ሲሉ ገልጸዋል።

በስሜን ሸዋ ዞን የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪው አቶ ብርሃኑ አለበል” የገና ጨዋታ የየአካባቢው ነዋሪ የእርስ በርስ ትውውቅ የሚጎላበት፣ የማኅበረሰቡ ፍቅር የሚደረጅበት፣ ኅብረት የሚጠናከርበት፣ ቂም ከስሞ ሰላም የሚሰፍንበት ነው” ብለዋል።

በአማራ ክልል የባሕል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምንይችል ሙጨ “የገና ጨዋታ እድገት በማሳየቱ ጨዋታው ባሕላዊ ይዘቱን ሳይለቅ እንዲከናወን ሕግ እና ደንብ ተዘጋጅቶለታል” ብለዋል፡፡

የጨዋታው ሜዳ ቁመቱ 100 ሜትር ስፋቱ ደግሞ 90 ሜትር እንዲኾን ተደንግጓል ነው ያሉት፡፡ የማዕዘን መምቻው ክልልም በኖራ ይሰመራል፡፡

በዚህ ሜዳ ውስጥ ለመጫወት ሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች 15 ተጫዋቾችን ያቀርባሉ፡፡ 10ሩ ሜዳ ውስጥ ገብተው የሚጫወቱ ሲኾኑ አምስቱ ተቀያሪዎች ናቸው፡፡

የቡድኑ አሰላለፍ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ሁሉ ግብ ጠባቂ፣ ተከላካይ እና አጥቂ ተጫዋቾች ይኖሩታል፡፡ ጨዋታውን የሚመራ ዋና አጫዋች፣ የመስመር እዲሁም ተቀያሪ ተጫዋቾችን የሚቀይሩ ዳኞችም ይመደቡለታል፡፡

የሩሯ ክብደት እስከ 500 ግራም ከሚመዝን እንጨት፤ ከጠፍር ወይም ከፕላስቲክ ይዘጋጃል፡፡ የገናው ቁመት ከአንድ ሜትር መብለጥ የለበትም፡፡ ተጨዋቾቹ እኩል ቁመት ያለው የገና ዱላ እንዲይዙ ይገደዳሉ ብለዋል፡፡

ጨዋታው ሲጀመር ሁሉም ተጫዋቾች ተነፋነፍ የሚባለውን ባሕላዊ ልብስ ለብሰው ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ በጨዋታው ሕግ መሠረት ሩሯን በእግር እና በእጅ መንካት ነጥብ ያስቀንሳል፡፡ የጨዋታው የጊዜ ርዝማኔ 60 ደቂቃ ነው፡፡ 10 ደቂቃ ረፍት ይሰጣል፡፡

ጨዋታው ለዋንጫ ወይም ለደረጃ ከኾነ ቡድኖቹ ካልተሸናነፉ ተጨማሪ ደቂቃ እዲጫወቱ ይደረጋል፡፡ በዚህም ካልተሸናነፉ የቅጣት ምት እየተሰጣቸው እስኪ ሸናነፉ ድረስ ይጫወታሉ፡፡

የገና ጨዋታን የገና በዓል በሚከበርበት ወቅት ብቻ ከመጫወት ወጥቶ ልክ እንደ እግር ኳስ መዘውተር ቢችል እንደሚጠቅም ያላቸውን ምልከታ አቶ ምንይችል አጋርተዋል፡፡

የገና ጨዋታ ዳራ መጽሐፍን እና አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ በ2016 ዓ.ም የሠራውን ዘገባ በተጨማሪ ምንጭነት ተጠቅመናል።

መልካም በዓል!

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here