ልብ አንጠልጣዩ የዩናይትድ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል።

0
16

በሊዝበን በተካሄደው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አወዛጋቢ እና ትርምስ በበዛበት ጨዋታ ማንችስተር ዩናይትድ ከስፖርቲንግ ሊዝበን ጋር 2 ለ 2 በኾነ ውጤት ተለያይቷል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የዩናይትድ ግብ ጠባቂ ሴኔ ላሜንስ አንድ የፍጹም ቅጣት ምት ካዳነ ብዙም ሳይቆይ በአራውጆ ላይ በተሠራው ጥፋት የተሰጠውን ሁለተኛ ፍጹም ቅጣት ምት ሉዊስ ሱዋሬዝ አስቆጥሮ ስፖርቲንግን መሪ አድርጓል።

ከእረፍት በፊት አማድ ዲያሎ ያስቆጠረው የአቻነት ግብ ዳኛው ሲሞን ማርሲኒያክ ዩሪ ቲሌማንስ ጥፋት ሠርቷል በሚል ቀድመው ፊሽካ በመንፋታቸው ምክንያት በቪኤአር ሳይታይ ተሽሯል።

ከእረፍት መልስ በሦሥት ደቂቃዎች ውስጥ የቀድሞው የስፖርቲንግ ተጫዋች ብሩኖ ፈርናንዴዝ የምሽቱን ሦሥተኛ ፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥሮ ዩናይትድን አቻ አድርጓል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ፈርናንዴዝ የመታው ኳስ መሬት ነክቶ በመንጠር የስፖርቲንግን ግብ ጠባቂ ካይኬ ፔሬራን አልፎ መረብ ላይ በማረፉ ዩናይትድ መሪነቱን ጨብጧል።

ይሁን እንጂ የዩናይትድ ግብ ጠባቂ ላሜንስ የተሻማን ቀላል ኳስ መያዝ ተስኖት በመጣሉ ሉዊስ ሱዋሬዝ በመቀስ ምት ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሮ ጨዋታውን አቻ አድርጓል።

በጨዋታው መገባደጃ ላይ የስፖርቲንግ ግብ ጠባቂ ፔሬራ ኳስን በስህተት ወደ ራሱ መረብ ቢያስገባም ዳኛው ቪኤአርን ከተመለከቱ በኋላ ፓትሪክ ዶርጉ ጥፋት ሠርቷል በሚል ግቡን ሽረውታል። በጭማሪ ሰዓት ላይም ዩሪ ቲሌማንስ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ በመወገዱ ዩናይትድ በዳኝነት ውሳኔዎች ቅሬታ እያሰማ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተገዷል።

በሌላ ጨዋታ ሊቨርፑል ከሜዳው ውጭ በያን ብሬይደል ስታዲየም የቤልጂየሙን ክለብ ብሩዥ ገጥሞ 3 ለ 0 አሸንፏል።

ለሊቨርፑል አሌክሳንደር ኢሳክ(ሁለት) እና ፍሎሪያን ዊርትዝ የድል ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሊቨርፑል በ12 ነጥብ አምስተኛ እንዲሁም ክለብ ብሩዥ በ9 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በፓርክ ደ ፕራንስ ሮማን ያስተናገደው ፒኤስጂ 2 ለ 2 ተለያይቷል።

ፒኤስጂ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ አቻውን ባስመዘገበበት በዚህ ጨዋታ ኢሊያ ዛባርኒ እና ኡስማን ዴምቤሌ (በፍፁም ቅጣት ምት) ለፒኤስጂ፣ እንዲሁም ማሪዮ ሄርሞሶ እና ዶኒዬል ማሌን (በፍፁም ቅጣት ምት) ለሮማ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ከአምስት ጨዋታዎች 13 ነጥብ የሰበሰበው ፒኤስጂ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ሮማ በ5 ነጥብ 25ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሌሎች ጨዋታዎች፦

አትሌቲኮ ማድሪድ 2 – 0 ቫይኪንግ

ኢንተር ሚላን 2 – 0 ስቱትጋርት

ሊል 2 – 1 ባየር ሙኒክ

ሻክታር ዶኔትስክ 0 – 1 ፌነርባቼ አሸንፈዋል።

#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ኅዳር_17_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here