በአሠልጣኝ ቶማስ ቱሄል የምትመራው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን፣ የዓለም ዋንጫ ባለቤቷን ስፔን በማድሪድ ሜትሮፖሊታኖ ስታዲየም 3 ለ 2 በኾነ ውጤት በማሸነፍ የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ምድቧን በአንደኝነት መምራት አስችሏታል።
በጨዋታው መጀመሪያ የበላይነት የወሰደችው እንግሊዝ፣ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ፓው ኩባርሲ በሃሪ ኬን ላይ የሠራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ሃሪ ኬን 93ኛ ዓለም አቀፍ ግቡን በማስቆጠር መሪ ኾናለች።
ከእረፍት መልስ በ53ኛው ደቂቃ ኤዝሪ ኮንሳ ከዴክላን ራይስ የተሻማውን የማዕዘን ምት በጭንቅላቱ በመግጨት ሁለተኛውን ግብ ሲያክል፣ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቤን ዋይት ሦሥተኛዋን ግብ በማስቆጠር የእንግሊዝን መሪነት አስፍቷል።
ይሁን እንጂ በ65ኛው ደቂቃ ጃሬል ኮንሳ ኳስ መነጠቁን ተከትሎ ኤሊዮት አንደርሰን በላሚን ያማል ላይ በሠራው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ መወገዱ የጨዋታውን መልክ ቀይሮታል።
የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ሚኬል ኦያርዛባል ወደ ግብ ሲቀይረው፣ በ75ኛው ደቂቃ ደግሞ ከላሚን ያማል የተሻገረለትን ኳስ ተቀይሮ የገባው ኒኮ ዊሊያምስ በማስቆጠር ልዩነቱን ወደ አንድ አጥብቧል።
በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ስፔን አቻ ለመኾን ከፍተኛ ጫና ብትፈጥርም፣ የእንግሊዙ ግብ ጠባቂ ጄምስ ትራፎርድ ተከታታይ አስደናቂ ኳሶችን በማዳን ቡድኑን ለድል አብቅቷል።
ይህ ውጤት ስፔን ከመጋቢት 2024 እ.ኤ.አ ወዲህ በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሳትሸነፍ የቆየችበትን የ43 ጨዋታዎች ሪከርድ የገታ ኾኗል።
በሌሎች ጨዋታዎች ቤልጀም ጣሊያንን 4 ለ 1 በኾነ ሰፊ ውጤት ስታሸንፍ ፈረንሳይ ቱርክን እና ክሮሽያ ቸክ ሪፐፕሊክን በተመሳሳይ ውጤት 2 ለ 1 ፤ አልባኒያ ቤላሩስን 2 ለ 0 ፤ ፊላንድ ሳማሪኖን 7 ለ 2 ፤ ሞንቴኔግሮ ሲፕረስን 4 ለ 1ሲያሸንፉ አርመኒያ እና ላቲቪያ ያለግብ ተለያይተዋል።
#አሚኮ #ስፖርት🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ኅዳር_07_2019_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



