የቀድሞው የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በ2027 መጋቢት ወር በሚካሄደው የፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ እያጤኑ መሆኑን ቢቢሲ አስነብቧል።
በፊፋ ውስጥ የአለም አቀፍ የእግርኳስ ልማት ሀላፊ በመሆን እየሰሩ ያሉት የ77ዓመቱ ፈረንሳይ የጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተፎካካሪ በመሆን ለፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ሲገለፅ የቆየ ቢሆንም ቬንገር በዚህ ጉዳይ በግልፅ ሀሳባቸውን ከመስጠት ተቆጥበው ቆይተዋል።
አሁን ላይ እየወጡ ባሉ መረጃዎች ግን የቀድሞው የአርሰናል አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር በፊፋ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የጂያኒ ኢንፋንቲኖ ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ እያሰቡ መሆኑ ተሰምቷል።
ቬንገር ለፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው እንዲቀርቡ በተለይ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ባለስልጣናት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩም ይገኛል።
ምንም እንኳ የ77ዓመቱ አርሰን ቬንገር ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለረዥም ዓመታታ ፊፋን በፕሬዝዳንትነት ላይመሩ እንደሚችሉ ቢጠበቅም አንድ ተርም /አራት አመትም ቢሆን ተቋሙን እንዲመሩ ደጋፊዎቻቸው አጥብቀው እየተመኙ ነው።
ኢንፋቲኖ የአለም ዋንጫን የንግድ ድርሻ ለግል ባለሀብቶች ለመሸጥ ባደረጉት ያልተሳካ እቅድ ምክንያት ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ይታወቃል።
ያልተሳካውን የኢንፋቲኖ እቅድ በተመለከተ ቀደም ሲል ሀሳብ የሰጡት ቬንገግ በሀሳቡ እንዳልተሳተፉና ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ፕሮጀክቱ የሰማሁት በሚዲያ ነው ማለታቸው ይታወቃል።
የ56ዓመቱ ስዊዘርላንዳዊው አሁንም ቢሆን ከደቡብ አሜሪካ፣ አፍሪካ እና እስያ ድጋፍ እንዳላቸው ቢታመንም የአውሮፓ እግርኳስ መህበር ባለስልጣናት ግን ኢንፋቲኖ በቀጣዩ ምርጫ ከሀላፊነት እንዲለቁ ከፍተኛ ግፊት እያደረጉ ነው።
ሼንገር ተወዳዳሪ እጩ ሆነው የሚቀርቡ ከሆነ ኢንፋቲኖ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚጠብቃቸውም ቢቢሲ ጨምሮ ገልጿል።
ለፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ እጩዎች እስከ ፈረንጆቹ ህዳር 18 ተለይተው ይታወቃሉ።
የቀድሞው የቶተንሃም ተከላካይ ራሞን ቬጋ እና የጃፓን እግር ኳስ ማህበር የክብር ፕሬዝዳንት ኮዞ ታሺማም ቀደም ሲል በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ለመወዳደር ፍላጎት አሳይተዋል።
ኢንፋቲኖ ከፊፋ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እንደሚጨምር በቅርቡ ከገለፁ በኋላ በተላይ ከ54ቱ የካፍ አባል ሀገራት ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚኖራቸው ቢገለፅም ቬንገር ለአፍሪካ እግርኳስ ተጫዋቾች ካላቸው ክብርና ከሰጡት እድል አንፃር ከአህጉሩ ሀገራት ድጋፍ እንደሚኖራቸው ይታመናል።
ቬንገር የአርሰናል አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ለአፍሪካ ተጫዋቾች በሰጡት እድል ምክንያት የአፍሪካ ተጫዋቾች ሻምፒዮን በመባል የሚታወቁ ሲሆን የአለም ዋንጫ ተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 48 እንዲያድግና የአፍሪካ ሀገራት ቁጥር እንዲጨምር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ይህ ደግሞ ምንአልባት ለፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው የሚቀርቡ ቀሆነ የ77ዓመቱ ቬንገር ከአፍሪካ ሀገራት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል።
ባዘዘው መኮንን
አሚኮ #ስፖርት
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!



