ከአይን የራቀ ሁሉ ከልብ አይርቅም!! ሞ ሳላህ የቀየረው ከተማ እንጅ ወዳጅነት አይደለም።

0
6
አይዛክን ከሊቨርፑል ወደ ቱርክ ያደረሰው አስደናቂ ታሪክ
ግብፃዊው ኮከብ ሞሐመድ ሳላህ የዘጠኝ ዓመታት የሊቨርፑል ቆይታውን ቋጭቶ ከመርሲሳይድ ተሰናብቶ ወደ ቱርክ አቅንቷል። ነገር ግን ሳላህ ከሊቨርፑል ይዞት የሄደው አንድ የማይረሳ ወዳጅነት አለ።
የወልፍ-ሂርሽሆርን ሲንድሮም ተጠቂው አይዛክ ከርኒ፣ በትንሽ የፕላስቲክ ጊታሩ የሊቨርፑል ደጋፊዎችን መዝሙር በመዘመር የብዙዎችን ልብ የገዛ ልጅ ነው።
ሳላህና ቨርጅል ቫን ዳይክ በ2024 የገና ወቅት በድንገት ትምህርት ቤቱ በመገኘት ካስደሰቱት በኋላ የሁለቱ ወዳጅነት ይበልጥ ጠነከረ። ከዚያም አይዛክ በአንፊልድ የክብር እንግዳ ሆኖ መገኘት ጀመረ።
ሳላህ ወደ ትራብዞንስፖር ሲያቀና ግን ይህ ወዳጅነት እንዳይቋረጥ የቱርኩ ክለብ የማይረሳ ውሳኔ አደረገ። አይዛክና ቤተሰቡን በአየር ትኬት ወደ ቱርክ ጋብዞ፣ ከሳላህ ጋር እንደገና እንዲገናኙ አደረገ።
በአውሮፕላኑ ውስጥ አይዛክ ብርቱካን ጭማቂውን እየጠጣ የቱርክን ባህል የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ሲመለከት፣ የበረራ አስተናጋጇ የሳላህን ስም የያዘ አዲሱን የትራብዞንስፖር ማሊያ ይዛ ቀረበችለት።
የአይዛክ ዓይኖች በደስታ በሩ። የጉዞው ዋና ዓላማ ግን ማሊያው ብቻ አልነበረም። ከሊቨርፑል ወደ ቱርክ፣ ከአንፊልድ ወደ ትራብዞን የተደረገው ይህ ልዩ ጉዞ አይዛክን ከቀድሞ ጀግናው ሞሐመድ ሳላህ ጋር እንደገና አገናኘው።
ሁለቱም በድጋሚ ተገናኝተው በፍቅር ተቃቀፉ።
ሳላህ ክለብ ቀይሮ ሊሆን ይችላል፤ ከተማ ቀይሮ ሊሆን ይችላል። ይህ ታሪክ ግን እግር ኳስ ከግብና ከዋንጫ በላይ የሆነ የሰው ልጅ ፍቅርና ወዳጅነት እንዳለው ያሳየናል።
ዳናይት ሲሳይ
#ባሕር_ዳር፡ ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here