ለ25ኛ ግራንድስላም ክብር እየተንደረደረ የሚገኘው ኖቫክ ጆኮቪች !

0
35
በእንግሊዝ አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው የዌምብልደን ቴኒስ ውድድር የወንዶች ሩብ ፍጻሜ ትንቅንቅ ትላንት ተጠናቅቆ ግማሽ ፍጻሜ የደረሱ ተጫዋቾች ታውቀዋል።
የ24 ጊዜ የግራንድስላም ሻምፒዮኑ ሰርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች በታሪክ ብቸኛ ረጅም ስኬት ያስመዘገበበትን 25ኛ ዋንጫ ለማንሳት የ1 የግራንድስላም ድል ብቻ ይቀረባዋል።
በለንደን ሴንተር ሜዳ በተደረገው በዚህ ጨዋታ የ39 ዓመቱ ጆኮቪች በ14 ዓመት ከሚያንሰው ካናዳዊው ፌሊክስ ሀገር-አሊያስሜ ጋር ያደረገው ጨዋታ አስደናቂ እና እጅግ ፈታኝ የነበረ ሲኾን፣ 5 ሰዓት ከ15 ደቂቃ በመውሰድ በዌምብልደን ታሪክ ረጅሙ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ኾኖ ተመዝግቧል።
የመጀመሪያውን እና የመጨረሻውን ወሳኝ አምስተኛ ዙር 7 ለ 6 በኾነ አቻ ውጤት ጨምሮ ጆኮቪች ተጋጣሚውን 3 ለ 2 በኾነ ድምር ውጤት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሻግሯል።
ምንም እንኳ ከዕድሜው መግፋት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ አስተያየቶች ምላሽ የሰጠበት ጨዋታ ቢኾንም በጨዋታው መጀመሪያ ላይ የገጠመው የግራ እግር ጡንቻ መሳሳብ ጉዳት የሕክምና እረፍት እንዲወስድ አስገድዶታል።
ጆኮቪች ከድሉ በኋላ በሰጠው አስተያየት “ይህ ጨዋታ ለእኔ ልክ እንደ ፍጻሜ ጨዋታ ነበር፤ ያለኝን አቅም በሙሉ ሰጥቻለሁ” ብሏል።
በግራንድስላም ውድድሮች ለ55ኛ ጊዜ፣ በዌምብልደን ደግሞ ለ15ኛ ጊዜ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰው ጆኮቪች በመጭው አርብ የዓለም ቁጥር አንዱን ጣሊያናዊውን ያኒክ ሲነር ይገጥማል።
ሲነር ባለፉት አራት የዌምብልደን ፉክክሮቹ አንድም ዙር ሳይሸነፍ ለዚህ ዙር የበቃ ጠንካራ ተፎካካሪ ነው።
ሁለቱ ተጫዋቾች ከ2021 ጀምሮ 11 ጊዜ የተገናኙ ሲኾን ሲነር 6 ጊዜ፣ ጆኮቪች ደግሞ 5 ጊዜ አሸንፈዋል። ለመጨረሻ ጊዜ በ2026 አውስትራሊያን ኦፕን ሲገናኙ ጆኮቪች 3 ለ 2 በኾነ ጠባብ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
ሁለቱም ቀኝ እጃቸውን የሚጠቀሙ እና ተመሳሳይ የአጨዋወት ዘይቤ ያላቸው በመኾኑ አሁን ላይ የጆኮቪች የአካል ብቃት የሲነርን ጠንካራ ምቶች ለመቋቋም ምን ያህል ዝግጁ ነው የሚለው ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል።
በሐናማርያም መስፍን
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here