ኦሊቨር ግላስነር የኖቲንግሃም ፎረስት ዋና አሠልጣኝ ኾነው ተሾሙ።

0
50

 

ኖቲንግሃም ፎረስት ኦሊቨር ግላስነርን አዲሱ ዋና አሠልጣኝ አድርጎ በይፋ መሾሙን አስታውቋል። ግላስነር የክለቡን የቴክኒክ ክፍል በመረከብ የ2026/27 የውድድር ዘመንን እንዲመሩ ተሹመዋል።

አዲሱ አሠልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ከዚህ ቀደም በክሪስታል ፓላስ ባሳዩት አስደናቂ የዋንጫ ስኬት እና የጨዋታ አቀራረብ የሚታወቁ ናቸው። ያንን የተሳካ የቡድን አደረጃጀት ወደ ኖቲንግሃም ፎረስት ይዘው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው የውድድር ዘመን (2025/26) ኖቲንግሃም ፎረስት በፕሪሚየር ሊጉ ከመውረድ አምልጦ ለመቆየት በነበረው ከፍተኛ ትግል የተነሳ እጅግ ያልተረጋጋ ነበር። ምንም እንኳን በሊጉ ለህልውናው ቢታገልም ክለቡ በኢሮፓ ሊግ ደግሞ አስደናቂ ብቃትን በማሳየት እስከ ግማሽ ፍጻሜ መድረስ ችሏል።

ይህ ያልተረጋጋ የውጤት ሂደት ከአሠልጣኞች መፈራረቅ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሲኾን በውድድር ዘመኑ ክለቡ አራት የተለያዩ ቋሚ አሠልጣኞችን በመቀያየር የፕሪሚየር ሊጉን ታሪክ ሰብሯል። እያንዳንዱ አሠልጣኝ በቆይታው የነበረው የጨዋታ መሪነት መረጃ የሚከተለው ነው።
ኑኖ ኤስፒሪቶ ሳንቶ 4 ጨዋታዎች
አንጌ ፖስትኮግሎ 6 ጨዋታዎች
ሾን ዳይች 18 ጨዋታዎች
ቪቶር ፔሬራ 12 ጨዋታዎች

የክለቡ ባለቤት ኢቫንጌሎስ ማሪናኪስ በክለቡ አሥተዳደር ላይ የወሰዷቸው ቀጥተኛ ውሳኔዎች ለአሠልጣኞች አለመረጋጋት መፈጠር ዋነኛው ምክንያት እንደኾነ ተገልጿል።

ለክለቡ የኢሮፓ ሊግ ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ የነበረው ኤሊየት አንደርሰን መልቀቅ በክለቡ ላይ ክፍተት ፈጥሯል። አዲሱ አሠልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ለኤሊየት አንደርሰን ተተኪ መፈለግ የዘንድሮው የክለቡ ዋነኛ የዝውውር እና የአሠልጣኝነት ሥራቸው እንደሚኾን ይጠበቃል ሲል ስካይ ስፖርት አስነብቧል።

በጥበቡ ሰለሞን

#አሚኮ_ዜና#ስፖርት
#ባሕር_ዳር_ሰኔ29_2018ዓ_ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here