⚽️ የፈረንሳይን ብሔራዊ ቡድን የሚገታው ማነው ?

0
9

 

ባሕር_ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም ⚽️ በአሠልጣኝ ዲዲየር ዴሻምፕ የሚመራው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ሁሉ አስደናቂ ብቃት እያሳየ ይገኛል።

ትናንት ምሽት ከሲዊዲን ጋር በኒውጀርሲ ያደረገውን ጨዋታ 3 ለ 0 በኾነ ሰፊ ውጤት በመርታት ግስጋሴውን ቀጥሏል።

በጨዋታው ኪሊያን ምባፔ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በውድድሩ ያስቆጠራቸውን አጠቃላይ ግቦች ቁጥር ወደ ስድስት ማሳደግ ችሏል። ቀሪዋን አንድ ግብ ብራድሊ ባርኮላ ከመረብ አሳርፏል።

ፈረንሳይ በምድብ ጨዋታዎች ሴኔጋልን 3 ለ 1፣ ኢራቅን 3 ለ 0፣ ኖርዌይን 4 ለ 1 በመርታት ለተከላካይ መስመር እረፍት የማይሰጥ ቡድን መኾኑን እያስመሰከረ ይገኛል።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ፈረንሳይ እያሳየች ያለውን ድንቅ ብቃት መግታት የሚችለው አንድ ብሔራዊ ቡድን ብቻ እንደኾነ የእግር ኳስ ተንታኝ እና የቀድሞው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተከላካይ ጋሪ ኔቪል ገልጿል።

ጌሪ ኔቪል በሰጠው አስተያየት በአሁኑ ወቅት ከፈረንሳይ ጋር መወዳደር የሚችል ብቃት ያለው ብቸኛው ቡድን አርጀንቲና ብቻ እንደኾነ ጠቁሟል።

አርጀንቲናም በተመሳሳይ በምድቧ ያደረገቻቸውን ሦሥት ጨዋታዎች በድል አጠናቅቃ በጥሎ ማለፉ ኬፕ ቨርድን ለመግጠም እየተዘጋጀች ትገኛለች።

ሜትሮ ስፖርት እንደዘገበው “በአሁኑ ሰዓት ፈረንሳይን ከዓለም ዋንጫ ሻምዮናነት ሊያስቆም የሚችለው ብቸኛው ቡድን አርጀንቲና ብቻ ነው፤ ይህን ያልኩበት ምክንያት የአርጀንቲና ተጫዋቾች ያላቸው የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና፣ በሜዳ ላይ የሚያሳዩት ጠንካራ ፉክክር እና የካበተ ልምድ ያላቸው በመኾኑ ነው”ብሏል።

እንደ እንግሊዝ፣ ስፔን እና ፖርቱጋል ያሉ ቡድኖች ወደፊት ብቃታቸውን አሳድገው ሊመጡ እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ ያለዉ ኔቭል ፈረንሳይ ከሌሎቹ ቡድኖች እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ ስለምትገኝ ዋንጫውን ካላነሳች ራሷን እንደጎዳች ነው የምቆጥረው ብሏል።

ምባፔ፣ ባርኮላ፣ ኡስማን ዴምቤሌ እና ማይክል ኦሊሴን ያካተተውን የፈረንሳይ የፊት መስመር አድንቋል።

“ይህ የፊት መስመር ጥምረት ለማንኛውም ተከላካይ አስፈሪ ነው፤ እንዴት ሊያስቆሟቸው እንደሚችሉም አላውቅም። ብራዚል በመጨረሻዋ ደቂቃ ስታሸንፍ፣ ጀርመን እና ኔዘርላንድስ ደግሞ ከውድድሩ ተሰናብተዋል። ፈረንሳይ ግን በዚህ የዓለም ዋንጫ እንዴት መጫወት እንዳለባት ለዓለም እያሳየች ነው” ብሏል።

#አሚኮ_ዜና #ዓለም_ዋንጫ🌏#ስፖርት⚽️

በሀብታሙ ዳኛቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here