በዓለም ዋንጫ የመጫወት ህልሙን ያሳካው ስደተኛ ተጫዋች

0
53

 

ደብረ ብርሀን : ሰኔ7/2018ዓ.ም.(አሚኮ) ኔስቶሪ ኢራንኩንዳ ስሙን በአውስትራሊያ የእግር ኳስ ታሪክ በደማቁ ጽፏል።

ይህ ስኬቱ ድንገተኛ ሳይሆን አስቀድሞም ቢሆን ራሱ በትጋት የጻፈው የአስደናቂ ታሪኩ ውጤት ነው።

ይህ የ20 ዓመቱ የዋትፎርድ አጥቂ አውስትራሊያ ቱርክን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት በረታችበት ጨዋታ የመክፈቻዋን ጎል በ27ኛዉ ደቂቃ በማስቆጠር በዓለም ዋንጫ ታሪክ ለአዉስትራሊያ በትንሽ ዕድሜዉ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ተጨዋቹ ጨዋታው እንደተጠናቀቀ በሰጠው አስተያየት “ይህ ከእውነት የራቀና ህልሜ እውን የሆነበት ትልቅ አጋጣሚ ነው” ሲል ስሜቱን ገልጿል።

የኢራንኩንዳ የህይወት ጉዞ ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር። እ.ኤ.አ. በ2006 በታንዛኒያ የስደተኞች ካምፕ የተወለደው ይህ ተጫዋች ወላጆቹ በአገራቸው በነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ከብሩንዲ የተሰደዱ ነበሩ።

ወላጆቹ የተሻለ ህይወትን ፍለጋ ህጻኑን ኢራንኩንዳ ይዘው ወደ አውስትራሊያ ያቀኑ ሲሆን ዛሬ ላይ ግን ያ በስደት ያደገው ህጻን በትልቁ የዓለም እግር ኳስ መድረክ ላይ አውስትራሊያን ወክሎ ታሪክ ለመስራት በቅቷል።

በአውስትራሊያ ሊግ በአደላይድ ዩናይትድ ደምቆ የታየው ኢራንኩንዳ፣ እ.ኤ.አ. በ2024 ወደ ጀርመኑ ሀያል ክለብ ባየርን ሙኒክ ቢያቀናም የመሰለፍ እድል አላገኘም ነበር። በክለቡ የመሰለፍ እድል ማጣቱ ደግሞ በዓለም ዋንጫው ላይ ለአውስትራሊያ የመጫወት ትልቅ ህልሙን አደጋ ላይ ጥሎት ነበር።

ተጫዋቹ እ.ኤ.አ. በሰኔ 2024 በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከባንግላዲሽ ጋር በተደረገ ጨዋታ ለብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን አድርጓል።

ይሁን እንጂ በባየርን ሙኒክ በነበረዉ ቆይታ የመሰለፍ እድል ሳያገኝ በስዊዘርላንዱ ግራስሆፐር በውሰት ካሳለፈ በኋላ ከባድ የተባለውን ውሳኔ ለመወሰን ተገዷል።

ባየር ሙኒክን በመልቀቅም ባልተረጋገጠ የዝውውር ዋጋ ወደ የእንግሊዙን ዋትፎርድ ተቀላቅሏል።

ኢራንኩንዳ ለስካይ ስፖርት በሰጠው ቃለምልልስ “ከባድ ውሳኔ ነበር የወሰንኩት፤ ነገር ግን ለእኔ ትልቁ ዓላማዬ በዓለም ዋንጫ ላይ መጫወት ነበር” ይላል።

“የ2026 የዓለም ዋንጫ ሊጀምር የቀረዉ ጥቂት ጊዜ ነበር፤ እኔ ደግሞ የመጫወቻ እድል ማግኘት ነበረብኝ ምክንያቱም በባየርን ሙኒክ እየተጫወትኩ አልነበረም። በሌላ በኩል በእንግሊዝ መጫወት ሁልጊዜም ህልሜ ነበር” ሲል ውሳኔውን ያስረዳል።

ወጣቱ አጥቂ ኢራንኩንዳ በአውስትራሊያ እግር ኳስ ታሪክ በአለም ዋንጫ ለአዉስትራሊያ በትንሽ እድሜዉ ጎል ያስቆጠረ ተጫዋች በመሆን ታሪክ ሰርቷል።

በ20 ዓመት ከ124 ቀናት ዕድሜው ድንቅ ጎል ያስቆጠረው ይህ ኮከብ ብሬት ሆልማን እ.ኤ.አ. በ2010 በዓለም ዋንጫ ላይ በጋና መረብ ላይ በ26 ዓመት ከ84 ቀናት ዕድሜው ለአዉስትራሊያ ጎል በማስቆጠር አስመዝግቦት የነበረውን የ16 ዓመታት ክብረ ወሰን አሻሽሎታል።

ሀብታሙ ዳኛቸዉ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here