ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዛሬ በግሪጎሪያውያኑ ዘመን አቆጣጠር ሰኔ 5 ቀን በዓለም እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ሜዳ ላይ ባለው የማይበገር ወኔ፣ ብረት በለበሰ ጽናቱ እና አስደናቂ ጉልበቱ የሚታወሰው የኮትዲቯሩ አማካይ ቼክ ቲዮቴ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየበት መታሰቢያ ዕለት ነው።
እ.አ.አ በ2017 በዚህች ዕለት ነበር በቻይና ቤጂንግ ኢንተርፕራይዝስ ክለብ ልምምድ ላይ እያለ በድንገት ልቡ ቆሞ በ30 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈው። ቲዮቴ በወጣትነቱ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም ያሳለፈው የሕይወት ጉዞ ግን ከምንም ተነስቶ ዓለምን ማሸነፍ እንደሚቻል የሚያሳይ እውነተኛ ማሳያ ነው።
የቼክ ቲዮቴ የሕይወት መጀመሪያ እጅግ ፈታኝ እና ልብ የሚነካ ነበር። በኮትዲቯር ያሙሱክሮ ከተማ ሲያድግ እስከ 15 ዓመቱ ድረስ የራሱ የእግር ኳስ ጫማ እንኳ አልነበረውም፤ ጨዋታዎችን ሁሉ ያደርግ የነበረው በባዶ እግሩ ነበር።
ኾኖም በውስጡ ያለው የኳስ ፍቅር እና ታላቅ ብቃት ተሸሽጎ አልቀረም። በጽናቱ እና በትጋቱ ተመልምሎ እ.አ.አ በ2005 ወደ አውሮፓ በማምራት ለአንደርሌክት መጫወት የጀመረ ሲኾን በኋላም ወደ ደቹ ትዌንቴ አምርቶ የሆላንድ ሊግ ሻምፒዮን መኾን ችሏል።
የእግር ኳስ ሕይወቱ ትልቁ ምዕራፍ የተጻፈው እ.አ.አ በ2010 ወደ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በመምጣት ኒውካስትል ዩናይትድን በተቀላቀለበት ወቅት ነበር። በሊጉ ካሉ እጅግ ኃይለኛ፣ ኳስ አሳዳጅ እና አስፈሪ ተከላካይ አማካዮች አንዱ ለመኾን ጊዜ አልወሰደበትም። በሜዳ ላይ ያለው ቁርጠኝነት እና የትግል መንፈስ የኒውካስትል ደጋፊዎች የልብ ወዳጅ ያደረገው ሲኾን ለክለቡ በድምሩ 156 ጨዋታዎችን በታማኝነት አድርጎ አገልግሏል።
የቼክ ቲዮቴ ስም በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ሲነሳ ሁሌም ቀድማ የምትመጣው እ.አ.አ የካቲት 5/2011 በአርሰናል ላይ ያስቆጠራት ያች ተአምራዊ ጎል ናት። በዕለቱ አርሰናል ጨዋታውን 4 ለ 0 እየመራ የነበረ ቢኾንም፣ ኒውካስትሎች ተስፋ ሳይቆርጡ 3 ጎሎችን አከታትለው አስገቡ። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ከአርሰናል ተከላካዮች ተመልሳ የወጣችውን ኳስ ቲዮቴ ከሩቅ ርቀት በግራ እግሩ የመታው አስደናቂ ኳስ የአርሰናልን መረብ አናወጠው።
ጨዋታው 4 ለ 4 የተጠናቀቀ ሲኾን፣ ያች ግብ (ለኒውካስትል ያስቆጠራት ብቸኛ ግቡ) በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ታላቋ እና ፈጽሞ የማትረሳው ዘላቂ ትዝታ ኾና ተመዝግባለች።
በሀገር ደረጃም ቲዮቴ የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን (ዝሆኖቹ) የልብ ምት ነበር። በ2010 እና 2014 የዓለም ዋንጫዎች ላይ ሀገሩን በክብር የወከለ ሲኾን እ.አ.አ በ2015 ኮትዲቯር ታሪካዊውን የአፍሪካ ዋንጫ ስታነሳ እርሱ የቡድኑ ዋና የድል ምሰሶ እና መሪ ነበር። እንደ ቢቢሲ ዘገባ ቼክ ቲዮቴ ባዶ እግሩን ከመጫወት ተነስቶ የዓለምን መድረክ በጉልበቱ እና በጽናቱ ያሸነፈ፤ የቆሰለውን የቡድኑን ቅስም በሜዳ ላይ የሚጠግን እውነተኛ ታጋይ ነበር።
በጥበቡ ሰለሞን
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት_እግር_ኳስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



