የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የዓመቱ ምርጥ ወንድ ዕጩ ተጫዋቾችን ይፋ አደረገ።

0
79

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 28/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የዓመቱ ምርጥ የወንድ ተጫዋቾችን አውጥቷል።

የማንቸስተር ዩናይትዱ አማካይ ብሩኖ ፈርናንዴዝ በዚሁ እጩ ውስጥ ተካቷል። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የ31 ዓመቱ ብሩኖ ፈርናንዴዝ በእግር ኳስ ጸሐፊዎች ማኅበር የዓመቱ ምርጥ ወንድ እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማትን ማሸነፉ ይታወሳል።

ይህ የጸሐፊዎቹ ሽልማት አብዛኛውን ጊዜ ለፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን ለማሸነፍ ማን ቀዳሚ ተፎካካሪ እንደኾነ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ፖርቹጋላዊው አማካይ ዩናይትድ የውድድር ዓመቱን በሦስተኛ ደረጃ እንዲያጠናቅቅ ሚናው ከፍተኛ ነበር። በታሪክ ከፍተኛ የኾነ 21 ጎል የኾኑ ኳሶችን ማመቻቸትም ችሏል።

የአርሰናሎቹ አማካዩ ዲክላን ራይስ፣ ተከላካዩ ጋብሪኤል ማጋሌሽ እና ግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ሲያነሳ ለቡድኑ ስኬት ቁልፍ ተጫዋቾች ነበሩ ብሏል መረጃው። እነዚህ ተጫዋቾችም በዚሁ እጩ ውስጥ ሲካተቱ በሌላ በኩል የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሀላንድ እና የቡድን አጋሩ ቼርኪ በእጩነት ተካትተዋል።

የባለፈው ዓመት የሊቨርፑል አጥቂ የነበረው መሐመድ ሳላህ 29 ጎሎችን በማስቆጠር ቀያዮቹ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን እንዲያነሱ በማገዝ ሽልማቱን ማሸነፉ ይታወሳል።

የዚህ ውድድር አሸናፊዎች ነሐሴ 19/2018 ዓ.ም በማንቸስተር ከተማ በሚካሄደው 53ኛው ዓመታዊ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች ማኅበር የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ይፋ የሚደረጉ እና ክብር የሚሰጣቸው ይኾናል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

በቴዎድሮስ ኃይለ ኢየሱስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here