ባሕር ዳር፡ ግንቦት 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ለእግር ኳስ ውበት እና የአሸናፊነት መሠረት ከኾኑት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሚቆጠሩ ግቦች ናቸው፡፡
በርካታ ግብ ማስቆጠር የእግር ኳስ ውበት ብቻ ሳይኾን በአብዛኛው አንደኛውን ቡድን አሸናፊ እና ሻምፒዮን፤ ሌላውን ደግሞ ተሸናፊ ያደርጋል፡፡
በዓለም ዋንጫ ውድድር ግን ይህ ብዙ ጊዜ እንዳልሠራ ታሪክ ይነግረናል፡፡ በአንድ የውድድር መድረክ ከፍተኛ ግብ ያስቆጠሩ ሀገራትም ኾኑ በኮከብ ግብ አግቢነት የወርቅ ጫማ ተሸላሚ የኾኑ ተጫዋቾች ከሀገሮቻቸው ጋር ሻምፒዮን የኾኑበት አጋጣሚ በጣም ጥቂት ነው፡፡
ከተጫዋቾች አንጻር ስናየው እስከዛሬ ከተካሄዱት 22 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ለየብቻቸው በውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢነት አጠናቅቀው ከሀገራቸው ጋር ዋንጫውን ያነሱ ሁለት ተጫዋቾች ብቻ ኾነው እናገኛቸዋለን።
እነዚህም ተጫዋቾች አርጀንቲናዊው ማሪዮ ኬምፔስ እ.አ.አ (1978) እና ብራዚላዊው ሮናልዶ (2002) ናቸው፡፡
ከነርሱ ውጭ የተለየ ክስተት ያጋጠመው በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ላይ ነው፡፡ በወቅቱ ስድስት ተጫዋቾች በዕኩል አራት ግቦች የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ኾነው ሲያጠናቅቁ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ብራዚላዊያን ተጫዋቾች ከሀገራቸው ጋር ዋንጫውን አንስተዋል፡፡
ከዚያ ውጭ ኮከብ ግብ አግቢ የኾኑ ስድስት ተጫዋቾች ከሀገራቸው ጋር ለፍጻሜ ደርሰው እየተሸነፉ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቅቀዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ባለፈው የ2022ቱ የዓለም ዋንጫ በስምንት ግቦች የወርቅ ጫማውን የወሰደው ኬሊያን ምባፔ እነዚህ ግቦቹ ፈረንሳይን ለሻምፒዮናነት አለማብቃታቸው አሳዛኝ ኾኗል፡፡
በኮከብ ግብ አግቢነት አጠናቅቀው ነገር ግን ሀገራቸውን ቢያንስ እስከ ሦሥተኛ ላለው ደረጃ እንኳን ማብቃት ያልቻሉ ተጫዋቾችም ጥቂት አይደሉም፡፡ በዚህ ረገድ የ1994ቱ የዓለም ዋንጫ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡
በወቅቱ የሩሲያው ኦሌግ ሳሌንኮ እና የቡልጋሪያው ሂሪስቶ ስቶቺኮቭ ዕኩል ስድስት ግብ አስቆጥረው ሁለቱም የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ኾነዋል፡፡ነገር ግን ቡልጋሪያ በውድድሩ አራተኛ ደረጃን ይዛ ከማጠናቀቋ በቀር ሩሲያ ከምድቧ እንኳን ማለፍ አልቻለችም ነበር፡፡
እንደ ያሁ ስፖርትስ መረጃ በቡድን ደረጃ ሲታይም በ22ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ከተሳታፊ ሀገራት ሁሉ የመለያ ፍጹም ቅጣት ምቶችን ሳይጨምር በጨዋታ ከፍተኛ ግብ አስቆጥረው ሻምፒዮን የኾኑ ሀገራት የታዩት በዘጠኙ ውድድሮች ብቻ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡
ከእነዚህ ጥቂት መድረኮች አንዱ በኾነው እ.አ.አ የ1978ቱ የዓለም ዋንጫ አርጀንቲና እና ኔዘርላንድስ በበላይነት ዕኩል 15 ግቦችን በማስቆጠር ለፍጻሜ ተገናኝተው አርጀንቲና ሻምፒዮን ኾናለች፡፡
#አሚኮ_ዜና #ስፖርት #እግር_ኳስ
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ቤተሰብ ይሁኑ !
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !


