በእግር ኳስ ጨዋታ ደማቅ ታሪኳን ለማስቀጠል የተዘጋጀችው አፍሪካዊቷ ሀገር

0
5

 

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኳታር አስተናጋጅነት የተካሄደው ያለፈው የ2022ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር ለአፍሪካ እግር ኳስ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተበት ነበር፡፡በውድድሩ ሞሮኮ እስከ ግማሽ ፍጻሜ በመግባት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር መኾኗ ይታወሳል፡፡ የወቅቱ የሞሮኮ ታሪካዊ ጉዞ የእግር ኳስ ኃያላን የሚባሉ ታላላቅ የአውሮፓ ሀገራትን በማንበርከክ ጭምር የታጀበ ነበር፡፡

በውድድሩ ምድብ ስድስት ውስጥ የነበረችው ሞሮኮ በምድብ ጨዋታዎች ቤልጅየምን እና ካናዳን አሸንፋ ከክሮሺያ ጋር አቻ ተለያይታለች፡፡ በዚህም ሰባት ነጥብ በመያዝ በስድስተኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ የምድቧ መሪ ኾና ወደ ቀጣዩ ዙር አልፋ ነበር፡፡

በቀጣይ ሁለት ዙሮች ሁለት ታላላቅ የአውሮፓ ሀገራት ቢጠብቋትም ሁለቱንም በድል ተወጥታለች፡፡በጥሎ ማለፉ ዙር ከስፔን ጋር በተገናኘችበት ጨዋታ መደበኛውን 90 ደቂቃም ኾነ ተጨማሪውን ክፍለ ጊዜ ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ነበር ያጠናቀቁት፡፡

ወደ መለያ የፍጹም ቅጣት ምቶች ሲያመሩ ግን የሞሮኮ የበላይነት ያልተጠበቀ ነበር፡፡ ሁለት ምቶችን ያዳነው የግብ ጠባቂዋ ያሲን ቦኑ ብቃት ታክሎበት እና ስፔን አንድም ፍጹም ቅጣት ምት ማስቆጠር ተስኗት ሞሮኮ 3ለ0 አሸንፋ ማለፏ ይታወሳል፡፡

የአትላስ አናብስቱ ሩብ ፍጻሜ ላይ ሌላ የአውሮፓ ኃያል ሀገር ቢጠብቃቸውም እሱንም በድል ተወጥተዋል፡፡ የክርስቲያኖ ሮናልዶዋን ሀገር ፖርቹጋልን 1ለ0 አሸንፈው በዓለም ዋንጫ ታሪክ ግማሽ ፍጻሜ በመግባት የመጀመሪያ አፍሪካዊ ቡድን ኾነዋል፡፡

በርግጥ ሞሮኮ ከዚያ በኋላ በግማሽ ፍጻሜ በፈረንሳይ፣ በደረጃ ጨዋታ ደግሞ በክሮሺያ ተሸንፋ አራተኛ ደረጃን ይዛ ነው ያጠናቀቀችው፡፡

ኾኖም በታላቁ መድረክ አፍሪካን ከማኩራት ባለፈ በዓለም ዋንጫው ታሪክ ከደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ጋር ከአውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ ሀገራት ውጭ ግማሽ ፍጻሜ የገባች ሦስተኛዋ ሀገር ኾናለች፡፡

ዘንድሮም ያንን ደማቅ ታሪኳን ለማስቀጠል ያለመችው ሞሮኮ 26 ተጫዋቾችን የያዘ ጠንካራ ስብስቧን ይፋ አድርጋለች፡፡

በዚህ ስብስብ ውስጥ ላለፈው የዓለም ዋንጫ ገድሏ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ከኾኑት ተጫዋቾች መካከል ግብ ጠባቂውን ያሲን ቦኑን ጨምሮ የፒ ኤስ ጂው ተከላካይ አችራፍ ሀኪሚ እና የሪያል ማድሪዱ አጥቂ ብራሒም ዲያዝ አሁንም የቡድኑ ምሰሶዎች ናቸው፡፡
የካበተ ልምድ ያላቸው አንጋፋዎቹ ተጫዋቾች ሶፊያን አምራባት፣ ኑሴር ማዝራዊ፣ ሶፊያኔ ራሂሚ እና አብዲ ኢዛልዞሊም በቡድኑ ውስጥ ተካትተዋል፡፡

ሞሮኮ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከተደለደለችበት ምድብ ሦስት ከብራዚል ጋር በምታደርገው ፈታኝ ጨዋታ ውድድሯን የምትጀምር ሲኾን ሀይቲ እና ስኮትላንድ ሌሎች የምድቡ ሀገራት ናቸው፡፡

#አሚኮ #ስፖርት #ኢትዮጵያ-አፍሪካ🇪🇹

በኃይሌ አበራ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here