በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይደረጋሉ፡፡

0
36
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎በአፍሪካ ዋንጫው ኢትዮጵያን ጨምሮ የተሳታፊ ሀገራት ወደ ቀጣይ ዙር የማለፍ ዕጣ ፋንታ
በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይደረጋሉ፡፡
16 ሀገራት እየተሳተፉበት ባለው በዚሁ ውድድር ከአራቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ኾነው የሚያጠናቅቁ ሀገራት ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፉ ከአንደኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ የሚያገኙት ደግሞ በ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው ይሳተፋሉ፡፡
የመጀመሪያው ምድብ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታው ከግብጽ ጋር አቻ ተለያይቶ በሁለተኛ መርሐ ግብሩ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረበት ጎል በሞሮኮ 2ለ1 ተሸንፏል፡፡
ቀይ ቀበሮዎቹ ከሁለት ጨዋታ አንድ ነጥብ ብቻ ይዘው እና በስሌት ደረጃ አሁንም ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድል ኖሯቸው የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታ ዛሬ ምሽት 4፡00 ላይ በተመሳሳይ አንድ ነጥብ ካላት ቱኒዚያ ጋር ያካሂዳሉ፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ውስጥ ለመቆየት ብቻ ሳይኾን ከዓለም ዋንጫ ተሳታፊዎች ውስጥ የሚገባትን ዕድል ለማመቻቸት በዛሬው ጨዋታ የሚኖረው ብቸኛ ዕድል የግድ ጨዋታውን ማሸነፍ ይኾናል፡፡
ከምድቡ አስተናጋጇ ሞሮኮ እና ግብጽ ዕኩል አራት ነጥብ የያዙ ሲኾን ዛሬ ምሽት እርስ በእርስ በሚያደርጉት ጨዋታ አሸናፊው ሀገር ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን ያረጋግጣል፡፡አቻ ከተለያዩ ደግሞ ተያይዘው ያልፋሉ፡፡
ከምድብ ሁለት ያደረገቻቸውን ሁለት ጨዋታዎች ያሸነፈችው ኮትዲቯር አስቀድማ ማለፏን ስታረጋግጥ ካሜሩን እና ኡጋንዳ ዕኩል ሦሥት ነጥብ አላቸው፡፡ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ያለምንም ነጥብ መጨረሻ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ዛሬ ምሽት በሚካሄዱት የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች ኮትዲቯር ከኡጋንዳ፣ ካሜሩን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ተገናኝተው ሁለተኛው አላፊ ሀገር ይለያል፡፡
ከሦሥተኛው ምድብም እንዲሁ ሁለት ጨዋታዎችን ያሸነፈችው ታንዛኒያ አስቀድማ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ ማሊ ሁለት፣ ሞዛምቢክ እና አንጎላ ዕኩል አንድ ነጥብ አላቸው፡፡
ነገ ምሽት በሚካሄዱት የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች ሞዛምቢክ እና አንጎላ እርስ በእርስ ሲገናኙ ማሊ ማለፏን ያረጋገጠችውን ታንዛኒያን ትገጥማለች፡፡
ከመጨረሻው ምድብ አራት እስካሁን ማለፉንም ኾነ መሰናበቱን ያረጋገጠ ሀገር የለም፡፡ ከምድቡ አልጀሪያ አራት፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል እኩል ሦሥት ነጥብ፣ ጋና ደግሞ አንድ ነጥብ አላቸው፡፡
ነገ ምሽት በሚካሄዱት የመጨረሻ ጨዋታዎችም ማሸነፍ አሊያም አቻ ውጤት የሚያሳልፋት አልጀሪያ ሴኔጋልን ስትገጥም ደቡብ አፍሪካ ከጋና ይገናኛሉ፡፡
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ !
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here