አዲስ አበባ: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጋና አክራ በተካሄደው 24ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ 5 ወርቅ፣ 4 ብር እና 6 ነሐስ በድምሩ 15 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ሦሥተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል።
ሦሥተኛ ኾኖ ያጠናቀቀው የአትሌቲክስ ልዑክም እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶለታል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በሻምፒዮናው ሀገርን ያኮራ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ በምትታወቅባቸው ረዥም እና መካከለኛ ርቀቶች ከተመዘገበው ውጤት በተጨማሪ በአጭር ርቀት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ውድድር አቅም ያላቸውን ወጣቶች ለኦሎምፒክ እና ለዓለም ሻምፒዮና ለማብቃት ፌዴሬሽኑ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ሰፊ አቅም እንዳላት ያነሱት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በሁሉም የአትሌቲክስ ዘርፎች ብቁ እና ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት ይሠራልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አሥፈጻሚ አባል እና የልዑኩ ቡድን መሪ አበባ የሱፍ በጋና በነበረን ቆይታ ጥሩ ውጤት ለማምጣት እና የሀገርን ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ለማድረግ ሁሉም በከፍተኛ ኀላፊነት ስሜት ሠርቷል ብለዋል።
ተሳታፊ አትሌቶች ባገኙት ውጤት መሠረት የገንዘብ ሽልማት እና እውቅና ከፌዴሬሽኑ ተበርክቶላቸዋል።
ዘጋቢ፦ ባዘዘው መኮንን
#አትሌቲክስ- ስፖርት #ኢትዮጵያ🇪🇹
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



