በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያለመ ስፖርታዊ ውድድር በምዕራብ ጎጃም ዞን ተጀመረ።

0
20

 

ፍኖተሰላም፡ ግንቦት 9/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ዞናዊ የምዕራብ ሊግ የእግር ኳስ የክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል።

ውድድሩ በዞኑ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ክለቦች መካከል ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚካሄድ ነው።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ቡድን መሪ ምንውየለት ገበየሁ የምዕራብ ሊግ የክለቦች ውድድር በጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል።

ውድድሩ አሸናፊ ክለቦችን ለመለየት፣ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ያለመ መኾኑን አስረድተዋል።

ውድድሩ የእርስ በእርስ የልምድ ልውውጥ በማካሄድ ተቀዛቅዞ የቆየውን የስፖርት ዘርፍ ለማነቃቃት እንደሚያግዝም ነው የገለጹት።

በተለይ ስፖርታዊ ውድድሮች በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ የመገንባት ሚናቸው የጎላ በመኾኑ ሌሎች ውድድሮችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

አስተያየታቸውን ለአሚኮ የሰጡ ተጫዋቾች ተቋርጦ የቆየው የምዕራብ ሊግ ውድድር በመጀመሩ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። ስፖርት ከአልባሌ ቦታዎች ለመራቅ እና የእርስ በእርስ ግንኙነትን እንደሚያዳብር ገልጸው ውድድሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

በውድድሩ ማስጀመሪያ መርሐግብር የፍኖተሰላም ከተማ 01 ቀበሌ የእግር ኳስ ክለብ ከማንኩሳ የእግር ኳስ ክለብ ጋር የተገናኙ ሲኾን የፍኖተሰላም 01 እግር ኳስ ክለብ 3 ለ 1 አሸንፏል።

በውድድሩ ማጠቃለያ አሸናፊ የኾኑ ክለቦች ዞኑን በመወከል ለክልል ሊግ ተሳታፊ እንደሚኾኑ ተገልጿል።

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here