ታሪካዊው ዓለም አቀፍ የዱላ ቅብብል ውድድር በቦትስዋና ዛሬ ይጀመራል።

0
54

 

አዲስ አበባ፡ ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚስተናገደው እና ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው የዓለም የዱላ ቅብብል ውድድር ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በቦትስዋና አስተናጋጅነት ይጀመራል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ40 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ700 በላይ አትሌቶች በስድስት የውድድር ዓይነቶች ለድል እንደሚፋለሙ ይጠበቃል።

ትላንት አመሻሽ ላይ በተከናወነው የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት ዱማ ጊዲዮን ቦኮ ባስተላለፉት መልዕክት “እንኳን ወደ አልማዝ ሀብት ባለቤቷ ቦትስዋና በደህና መጣችሁ” ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ውድድሩ ታሪካዊ እንዲኾን ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ለአሸናፊዎች የሚሰጡት ሜዳሊያዎችም የሀገሪቱን ክብር በሚገልጽ መልኩ የአልማዝ ፈርጥ የያዙ መኾናቸውን ይፋ አድርገዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሰባስቲያን ኮ በበኩላቸው ቦትስዋና ለውድድሩ ያደረገችውን ዝግጅት በማድነቅ መድረኩ ዓለም የማይረሳው እንደሚኾን እና ለሀገሪቱ ለወደፊት ትልልቅ ኩነቶች እንደ መንደርደሪያ እንደሚያገለግል ዕምነታቸውን ገልጸዋል።

የዓለም እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች የሚሳተፉበት ይህ ግዙፍ መድረክ ዛሬ ከሰዓት 8:00 ጀምሮ የሚከናወን ሲኾን፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድብልቅ 4×400 ሜትር እና በሴቶች 4×400 ሜትር ይሳተፋሉ።

ከቻይናዋ ጓንግዡ መድረኩን የተረከበችው ቦትስዋና ውድድሩን በስኬት ለማጠናቀቅ በሀገሪቱ የፍቅር፣ የአክብሮት እና የመተሳሰብ መርህ ዝግጅቷን ማጠናቀቋ ተገልጿል።

ዘጋቢ፦ ሐናማርያም መስፍን

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here