“በራሪዋ ልዕልት”

0
69

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የበርሊንን ጎዳናዎች እንደ አቦ ሸማኔ ተምዘግዝጋባቸዋለች፤ በለንደን መንገዶች እንደነብር ተወንጭፋባቸዋለች። በበርሊን እንደ ኮከብ አሸብርቃለች፤ በለንደን እንደጮራ ደምቃለች።

ከእርሷ ጋር ሀገር ትሮጣለች፤ ከእርሷ ጋር ሠንደቅ ዓላማ ትቀድማለች፤ ከእርሷ ጋር ሀገር ትደምቃለች። በማይዋዥቅ ችሎታዋ፤ በማይደበዝዝ ፈገግታዋ ዓለምን አስደምማለች። ከፊት እየቀደመች የሀገሯን ሠንደቅ ዓላማ በዓለሙ ፊት ከፍ አድርጋለች፤ በስስት ለሚመለከቷት የሀገሯ ልጆች ደስታን እና ኩራትን ለግሳለች። እርሷን ለሚመለከቱ ጽናት ስኬትን እንደሚወልድ በተግባር አሳይታቸዋለች።

አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሠንደቅ በዓለም ሰማይ ሥር ከፍ ሲል ያን ጊዜ ኢትዮጵያ አብራ ከፍ ትላለች፤ ልጆቿ ሲስቁ አብራ ትስቃለች።

ቁጥራቸው የበዛ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለአረንጓዴ ቢጫ ቀዩዋ ሠንደቅ ዓላማ ክብር ታግለዋል። በእልህ እና በጀግንነት እየቀደሙ ኢትዮጵያን አኩርተዋል። ክብሯንም ከፍ አድርገዋል።

ይህን ካደረጉ ብርቅዬ አትሌቶች መካከል አትሌት ትዕግሥት አሰፋ አንደኛዋ ናት። ይህች ወጣት አትሌት አሁን ላይ የዓለምን ቀልብ ገዝታለች። የዓለም አትሌቲክስ ወዳጅ ሁሉ ስለ እርሷ እየተነጋገረ ነው።

ኢትዮጵያዊ ለዛ፤ ኢትዮጵያዊ ጽናት እና ጀግንነት የተላበሰችው አትሌቷ በዓለም የማራቶን ሩጫ አዲስ ታሪክ መጻፏን ቀጥላለች።

በጀርመን በርሊን በአስደናቂ ብቃት የታየችው ትዕግሥት በእንግሊዝ ለንደን ደግሞ ከቀደመው ልቃ እና ጠንክራ ታይታለች። የማራቶን ክበረ ወሰንን እየሰበረች፤ ስሟን እያደመቀች፣ ሀገሯን ኢትዮጵያን እያስጠራች ነው።

ትናንት በተደረገው የለንደን ማራቶን በራሪዋ ልዕልት የዓለም የሴቶች ማራቶንን ክብረ ወሰን በማሻሻል ድል አድርጋለች።

አትሌቲክስ ዊክሊ የተሰኘው ድረ ገጽ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ እስካሁን በተወዳደረችባቸው የማራቶን ውድድሮች ከአንደኛ እና ከሁለተኛ ደረጃ ውጭ ወጥታ አታውቅም ይላል። ትዕግሥት ካለች የወርቅ ሜዳሊያ ካልኾነ የብር ሜዳሊያ መውሰዷ አይቀርምና። አሁን ላይ በተፎካካሪዎቿ የምትፈራ፣ በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ደግሞ በጉጉት የምትጠበቅ ናት።

ትናንት በለንደን ሰማይ ሥር እንደ ጀንበር ያበራችው አትሌት ባለፈው ዓመት በለንደን ማራቶን ይዛው የነበረውን ክብረ ወሰን አሻሽላ ዳግም አሸንፋለች።

የለንደን ማራቶን በድረ ገጹ በለንደን ሰማይ ፀሐይ ደምቃለች፤ ነገር ግን የዓለም ክብረ ወሰኖች እንደ ዝናብ እየዘነቡ ነው በማለት የማራቶኑን ትንቅንቅ ገልጾታል። ስለ ምን ቢሉ በወንዶችም በሴቶችም የዓለም ክብረ ወሰን ተሰብሯልና።

እ.አ.አ በ2025 በለንደን ማራቶን 2 ሰዓት 15 ደቂቃ 50 ሴኮንድ በመግባት ዓለምን ጉድ ያስባለችው
ትዕግሥት አሰፋ ትናንት በተካሄደው ውድድር ደግሞ ሌላ ታሪክ ጽፋለች።

የባለፈው ዓመት ድሏን ያስጠበቀችው ትዕግሥት 2: ሰዓት 15 ደቂቃ 41ሴኮንድ በመግባት የራሷን ክብረ ወሰን አሻሽላለች። ከበፊቱም ጠንክራ ታይታለች።

ቢቢሲ በዘገባው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ክብሯን አስጠብቃ ድል አድርጋለች ብሏል።

ትዕግሥት ከድሉ በኋላ በሰጠችው አስተያየት በመጀመሪያ እግዚአብሔር ይመሥገን፤ ለዚህ ክብር ስላበቃኝ፤ የሴቶች የማራቶን ውድድር የዓለም ክብረ ወሰን መስበሬን ሳይ በጣም ነው ደስ ያለኝ ብላለች። የጠበኩት ሲሳካልኝ ደስ ብሎኛል፤ በጣም ከባድ ውድድር ነበር፤ ትንሽ ነፋስ ነበረው፤ ተፎካካሪዎቼም በጣም ጎበዞች ናቸው፤ ጥሩ ፉክክር ነው ያደረግነው ብላለች።

የዓለም አትሌቲክስ ደግሞ ታሪክ ራሱን ደግሟል ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ የራሷን ክብረ ወሰን በማሻሻል ድል አድርጋለች ብሏል።

አሁን የማራቶን በራሪዋ ልዕልት እርሷ ናት። እርሷ ካለች ድል አለ። እርሷ ካለች ክብረ ወሰን ማሻሻል እና አዲስ ታሪክ መጻፍ አለ።

ዘ ኢኮኖሚክስ ታይምስ በድረገ ገጹ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ከዓመታት በፊት በበርሊን ማራቶን አብርታ መታየቷን አስታውሷል።

ይህች አስደናቂ አትሌት የዓለም ክብረ ወሰንን ከመስበሯ አስቀድሞ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፏን ጽፏል። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ግን የዓለምን የማራቶን ታሪክ የቀየረች አስደናቂ አትሌት ለመኾን በቅታለች ይላል።

በጀርመን በርሊን የተጀመረው የበራራሪዋ ልዕልት ግስጋሴ በእንግሊዝ ለንደን የበለጠ ደምቋል፤ አሁን የዓለም በሴቶች ፈጣኗ አትሌት ናት። በአስደናቂ የብቃት ደረጃ ላይ የምትገኘው አትሌቷ በቀጣይም የሀገሯን ክብር ከፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል ይጠበቃል።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here