53 ቀናት የቀሩት የዓለም ዋንጫ ትውስታ እና የዛየር አይረሴ ክስተት

0
43
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለዘንድሮው የዓለም እግር ኋስ ዋንጫ ውድድር ተሳትፎ ከበቁ 10 የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር የአሁኑ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋ በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው ከዛሬ 52 ዓመታት በፊት በ1974ቱ መድረክ ነበር፡፡ ዛየር በሚለው የቀድሞ መጠሪያዋ ያደረገችው ያ ተሳትፎዋ ግን የጎል ጎተራ የኾነችበት እና በአዝናኝ ክስተት የታጀበ ኾኖ ያለፈ ነበር፡፡
በውድድሩ ከነበረችበት ምድብ በመጀመሪያ ጨዋታዋ በስኮትላንድ 2ለ0 ተሸነፈች፡፡በሁለተኛ ጨዋታዋ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ 9ለ0 በኾነ ሰፊ ውጤት ተረታች፡፡ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዋ ደግሞ ከብራዚል ጋር ነበር፡፡
ከዚያ ጨዋታ አስቀድሞ ታዲያ የወቅቱ የዛየር ፕሬዝዳንት ሞቡቱ ሴሴኮ ለተጫዋቾቻቸው እንዲህ የሚል አስገራሚ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
“ከብራዚል ጋር በምታደርጉት ጨዋታ አራት እና ከዚያ በላይ ጎል ገብቶባችሁ ከተሸነፋችሁ ወደ ሀገራችሁ እንዳትመለሱ! የሚል ነበር።
ጨዋታውን ብራዚል 2ለ0 እየመራች እያለ 78 ኛው ደቂቃ ላይ በዛየር የግብ ክልል አቅራቢያ አደገኛ በሚባል ቦታ ላይ የቅጣት ምት አገኘች፡፡
የብራዚል ተጫዋቾች የቅጣት ምቱን ለመምታት እየተመካከሩ እያለ ግን የዛየሩ ተከላካይ ጆሴፍ ምዌፑ ኦሊንጋ ድንገት ተንደርድሮ ኳሷን ጠለዛት፡፡
የተጫዋቹ ድርጊት የብራዚል ተጫዋቾች ፊሽካ ከተነፋ በኋላ የቅጣት ምቱን ፈጥነው ስላልመቱ ነው የሚል ቢመስልም ሀሳቡ ግን ጎሉ እንዳይቆጠር ጊዜ ለማባከን ነበር፡፡
በርግጥም ሀሳቡ ተሳክቶለታል፡፡ ዳኛው ቢጫ ካርድ እስኪሰጡት ቁጥሩን እና ስሙን እስኪመዘግቡ፣ የቅጣት ምቱን እንደገና እስኪያስመቱ ድረስ ቢያንስ ወደ አምስት የሚጠጉ ደቂቃዎች እንዲባክኑ አድርጓል፡፡
ቅጣት ምቱም ወደ ጎል ሳይቀየር ቀርቶ የኋላ ኋላ አንድ ጎል ተጨምሮ ጨዋታው በብራዚል 3ለ0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ የዛየር ተጫዋቾችም የፕሬዝዳንታቸውን ቃል አክብረው በብራዚል አራት እና ከዚያ በላይ ጎል ተቆጥሮባቸው ሳይሸነፉ በሰላም ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
አሁን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከዚያ አዝናኝ ክስተት 52 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫው በተመለሰችበት የዘንድሮው ውድድር በምድብ 11 ከፖርቹጋል፣ ከኡዝቤኪስታን እና ኮሎምቢያ ጋር በምታደርገው ፉክክር ውድድሯን ትጀምራለች ሲል ያስነበበው ያኾ ስፖርት ነው።
በኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here