ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ)
የዛሬ የዓለም ዋንጫ ትውስታችን 24 ዓመታትን ወደኋላ ተመልሶ ከ2002ቱ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውስጥ የ17ኛው የውድድር መድረክ ክስተትን ይቃኛል፡፡
የ2002ቱ የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር በጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ የጋራ አስተናጋጅነት ነበር የተካሄደው፡፡
በዚያ ውድድር የመክፈቻ ጨዋታ የተመዘገበው ያልተጠበቀ ውጤት የእግር ኳሱን ዓለም ያስደመመ ኾኖ ዛሬ ድረስ ይታወሳል፡፡ ከመጀመሪያው ምድብ በተካሄደው የመክፈቻ ጨዋታ የተገናኙት የ1998ቱ ውድድር አሸናፊ ፈረንሳይ እና ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው መድረክ የተከሰተችው ሴኔጋል ነበሩ፡፡
አፍሪካዊቷ ሀገር በዚያ ጨዋታ ታሪክ ትሠራለች ያለ ብዙም አልነበረም፡፡
በርግጥ በጨዋታው የመሐል ሜዳ ቴክኒሻኑ ዚነዲን ዚዳን በጉዳት ምክንያት ለፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን አልተሰለፈም፡፡እነ ቴሪ ኦንሪ፣ ማርሴ ዴሳሊና ፋቢያን ባርቴዝን የመሳሰሉ የወቅቱ ታላላቅ ተጫዋቾች ግን በቡድኑ ውስጥ ነበሩ፡፡
ጨዋታው ለግማሽ ሰዓት ያክል ያለጎል ከዘለቀ በኋላ በግራ ክንፍ በኩል የፍራንክ ሊቦፍን አደገኛ የማስጣል ሙከራ ያመለጠው የሴኔጋሉ አጥቂ አልሀጂ ዲዩፍ ያሻገራት ኳስ በርከት ካሉት የፈረንሳይ ተጫዋቾች አመለጠች። በማርሴ ዴሳሊ እግሮች መሐል አልፋ ፓፓ ቦባ ዲዮፕ ወደ ግብነት ቀየራት።
ከዚያ በኋላ ባሉት ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በሴኔጋል አሸናፊነት መጠናቀቁ ያለፈው ውድድር አሸናፊዋ በአዲስ ተሳታፊ ሀገር የተረታችበት የዓለም ዋንጫው ያልተጠበቀ አስደናቂ ውጤት ኾኖ ይታወሳል፡፡
አልሀጂ ዲዩፍ በወቅቱ ውጤቱን የዓለም ዋንጫው የምንጊዜም ታላቅ ድል ኾኖ ሊመዘገብ ይገባል ሲል የግቧ አስቆጣሪ ዲዮፕ በበኩሉ የእግር ኳስ ሕይወቴ ድንቅ ክስተት ሲል ገልጾታል፡፡
ከዚያ ጨዋታ በኋላ ፈረንሳይ በቀሪ የምድብ ጨዋታዎች በዴንማርክ ተሸንፋ እና ከኡራጓይ ጋር አቻ ተለያይታ በጊዜ ከውድድሩ ተሰናብታለች፡፡ በፈረንሳይ ድል የተበረታታችው ሴኔጋል ግን ግስጋሴዋ በዚያ አልተገታም፡፡
ያሆ ስፖርት እንደዘገበው ከምድቧ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፍ በጥሎ ማለፉ ከስዊድን ጋር ባደረገችው ጨዋታ በወቅቱ ተግባራዊ በነበረው እና በጭማሪ 30 ደቂቃዎች ቀድሞ ግብ ያስቆጠረ አሸናፊ ይኾናል በሚለው የጎልደን ጎል ሕግ አሸንፋ ወደ ሩብ ፍጻሜ አልፋለች፡፡
ሩብ ፍጻሜ ላይ ግን እሷም በተራዋ በቱርክ በጎልደን ጎል ተሸንፋ ያልተጠበቀ ግስጋሴዋ ተገትቷል፡፡
ዘጋቢ፦ ኃይሌ አበራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!



