1

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሀገራዊ የደን ሽፋንን ከማሳደግ እና ተፈጥሮን ከመታደግ አልፎ ሀገሪቱን በአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች ላይ በአህጉሪቱ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ እና ታማኝነት ካላቸው ድምጾች አንዷ እንድትኾን አድርጓታል።

ይህ በጥቂት ሀገራት ብቻ በሚታይ ግዙፍ ሀገራዊ የሕዝብ ንቅናቄ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ላይ የተመሰረተው ስኬት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ልማትን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ እና የለስላሳ ኅይል አካል እንድታደርግ አስችሏታል።

ለዚህም ማሳያው አንድ ቢሊዮን ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት በተለይም ለጂቡቲ፣ ለናይጀሪያ፣ ለሩዋንዳ፣ ለደቡብ ሱዳን እና ለሌሎችም ማካፈሏ ነው።

ስኬቱ በአፍሪካ ኅብረት፣ በኮፕ ጉባኤዎች እንዲሁም ከባህረ ሰላጤው እና ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ባላት የሁለትዮሽ ግንኙነት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ትሩፋቶችን እያስገኘላት እንደኾነ ከኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ድረ-ገጽ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ተፈጥሮ ድንበር ስለማይገድባት የአፍሪካ ቀንድን ከአየር ንብረት ቀውስና ከድርቅ ለመታደግ የኢትዮጵያ የደን ልማት ተሞክሮ እና ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት ማጋራት ወሳኝ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

ይህ የጋራ ሥነ-ምኅዳራዊ ጥበቃ ቀጣናዊ ደኅንነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ሀገራቱ ከተናጠል ጥረት ወጥተው በጋራ ጠላታቸው (በድህነት እና በአየር ንብረት መዛባት) ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያስችላቸዋል።

ከሥነ-ምኅዳራዊው ፋይዳው ባሻገር ይህ ተግባር ድንበር ተሻጋሪ የጋራ ልማትን እውን በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና አለው።

የጋራ ተፋሰሶችን በመንከባከብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ እና በሕዝቦች መካከል መተማመንን በመፍጠር ረገድ የተበረከቱት ችግኞች እንደ ዕውነተኛ የሰላም አምባሳደር ኾነው እያገለገሉ ነው።

በጋራ ዛፍ መትከል የቀጣናውን ትስስር ከመሠረተ ልማት (እንደ መንገድ፣ ባቡር እና ኤሌክትሪክ) ባለፈ በተፈጥሮ ጭምር በማስተሳሰር የጋራ የነገ ዕጣ ፈንታን ከመጋራት ጋር እኩል ትርጉም የሚሰጠው የረጅም ዘመን ራዕይ ነው።

የየደን ልማት አመራሩ ከጠንካራ የማረጋገጫ መሠረተ ልማት ጋር ያጣመረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ አህጉራዊ የካርበን አሥተዳደር ማዕቀፎችን ለመቅረጽ የተሻለ ቦታ ላይ ትገኛለች።

አፍሪካውያን በራሳቸው የተፈጥሮ ሀብት ላይ በሚተገበሩ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ላይ ውስን ተጽዕኖ ሲያሳድሩ የቆዩበትን ታሪክ በመቀየር አፍሪካ በአዳዲስ የዓለም አቀፍ አሥተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ሕግ ተቀባይ ሳትኾን ሕግ አውጭ እና አርቃቂ እንድትኾን ይህ ተግባር ሰፊ በር እንደከፈተላት የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል።

ይህ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በብዝኀ-ወገን መድረኮች በተከታታይ የሚያነሱት ሀገራዊ እና አህጉራዊ የስትራቴጂ ትልም አካል እንደኾነም አክሏል።

የተቀናጀ ጥረቱ ማሳረጊያ እና የዓለም አቀፍ ዕውቅና ማረጋገጫው ደግሞ ከተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) በ80ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ ላይ በዘላቂ የደን አያያዝ ዘርፍ የተገኘው ታሪካዊ ሽልማት ነው።

ይህ ዕውቅና ኢትዮጵያ በደን ሽፋን ፈጣን ዕድገት ያሳየችውን ተጨባጭ ልዕልና፣ በሕዝባዊ ንቅናቄ ያረጋገጠችውን የምግብ ዋስትና ትሩፋት እና ቀጣናውን ያስተሳሰረችበትን የላቀ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስኬት አጉልቶ አሳይቷል።

ሽልማቱ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠችው ትኩረት ጊዜያዊ ዘመቻ ሳይኾን ሀገርን ከጥፋት የመታደግ፣ አካባቢያዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና ለትውልድ ብሩህ ተስፋን የማውረስ ጥልቅ የሕልውና እና የልማት ራዕይ መኾኑን ለዓለም ሕዝብ በተጨባጭ አስመስክሯል።

ዛሬ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን በማዘጋጀት አርአያነቷን ለአለም እንድታስተምር ተደርጋለች። የኮፕ 32 ዝግጅቷንም ከወዲሁ ጀምራለች።

#አሚኮ #AMECO #GreenLegacy #ኢትዮጵያ #Ethiopia

#ባሕር_ዳር #ሕዳር_19_2019_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

Previous article🔋የነገዋ ኢትዮጵያ አሻራ እና ምሶሶ በጉባ ብሥራቶች!
Next article‎116 ዘመናዊ ካሜራዎች የተገጠሙለት የባሕር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲዬም እውነታዎች!