
ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2013ዓ.ም (አብመድ) ወቅቱ የጉንፋን በሽታ በስፋት የሚዛመትበት በመሆኑ መላው የዓለም ሕዝብ ከኮሮናቫይረስ እና ጉንፋን ጋር የሚጋፈጥበት ነው፡፡ በድርጅቱ የዓለም አቀፍ ተላላፊ በሽታዎች አደጋ ዝግጁነት ዳይሬክተር ሲልቪ ቢሪያንድ የጉንፋን በሽታ እንዳይዛመት አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ መክረዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ የጉንፋን ሕመምን ለመከላከል እና በኢንፍሎይንዛ አማካኝነት የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ መድኃኒት፣ ፀረ ቫይረስ እና መከላከያ ዘዴዎች አሉ። ይህም የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ያግዛል፡፡
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በግለሰቦች ደረጃ ተግባራዊ እንዲደረጉ የተላለፉ የጥንቃቄ መልእክቶች (አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ፣ አካላዊ ንክኪን ማስቀረት፣ አፍና አፍንጫን በእጅ አለመንካት) ጉንፋንን ለመከላከል ሁነኛ መፍትሔዎች መሆናቸውን ዳይሬክተሯ አመላክተዋል፡፡
ይህም ጉንፋን ቀደም ብሎ በተከሰተበት ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ተግባራዊ ተደርጎ ስርጭቱን እንደቀነሰው በተግባር ተረጋግጧል፡፡ በሰሜን ንፍቀ ክበብ የመኸር እና የክረምት ወቅት ተመሳሳይ እንደሚሆን በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም በተያዘው ዓመት የጉንፋን ስርጭት መለስተኛ ሊሆን እንደሚችል ተስፋ ይኖራል ብለዋል።
በዋናነት ግን የጉንፋንም እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምልክቶች ተመሳሳይ መሆናቸውን በመረዳት ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡ በወጣቶች ላይ በስፋት እየታዩ ያሉ ማሽተት አለመቻል እና ጣዕም አለመለየት ምልክቶች ግን በቀጥታ የኮሮናቫይረስ ምልክት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በተለይ ተያያዥ ሕመም ያለባቸው ሰዎች የደረት አካባቢ ሕመም፣ የመተንፈስ ችግር እና የመሳሰሉት ምልክቶች ከታዩባቸው የጤና ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ መልእክት አስተላልፈዋል።
በእርግዝና ጊዜ የነብሰ ጡሮች በሽታ የመቋቋም ሁኔታ ተለዋዋጭ ስለሚሆንም ለጉንፋን የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። በበሽታው እንዳይጠቁም ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል የበለጠ ጠንቃቃ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡ በተቻለ መጠን ሰው በሚበዛባቸው ቦታዎች እንዳይገኙ፣ ከተገኙም ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭነትን ለማስቀረት የተመከሩ የጥንቃቄ መልእክቶችን በተገቢው መንገድ እንዲተገብሩ ባስተላለፉት አጭር የቪዲዮ መልእክት መክረዋል።
በደጀኔ በቀለ
ምንጭ፡- የዓለም ጤና ድርጅት