የዓለም መገናኛ ብዙኀን የተቀባበሉት ብሥራት ከሞስኮ!

11

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በዡኮቭስኪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኾነው ኢትዮጵያ 12 የሩሲያ ሠራሽ ሱ-35 (Su-35) ዘመናዊ ተዋጊ ጀቶችን መረከቧን እንዲሁም አራት የኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን ለመታጠቅ መስማማቷን ይፋ ሲያደርጉ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሚዲያ ተቋማትን እና የወታደራዊ መረጃ ተንታኞችን ቀልብ በእጅጉ ስቧል።

ትልቁ የዓረብ ሚዲያ አል ጀዚራ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው ዘገባ “ወታደራዊ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የመከላከያ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል” ሲል ዘግቧል። በተጨማሪም የተዋጊ ጀት ስምምነቱ ሞስኮ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የጸጥታ እና የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጥበቅ እና ስትራቴጂካዊ አጋርነቷን ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት ትልቅ ማሣያ መኾኑን ገልጿል።

ይህም እ.ኤ.አ በ2021 በሁለቱ ሀገራት መካከል በአዲስ አበባ የተፈረመውን የወታደራዊ ትብብር ስምምነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ መኾኑን አስታውሷል።

ታዋቂው የዜና ወኪል ሮይተርስ በበኩሉ የሩሲያው የመከላከያ ምርቶች ላኪ ድርጅት ሮሶቦሮን ኤክስፖርት የመጀመሪያዎቹ ተዋጊ ጀቶች ለኢትዮጵያ አየር ኀይል መሰጠታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተዋጊ ጀቶቹ ከታቀደው ጊዜ በአንድ ዓመት ቀድመው መድረሳቸውን እንዳሳወቁ ጠቅሶ ይሄው ስኬት የተመዘገበው በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ልዩ ቁርጠኝነት እና ድጋፍ መኾኑን ገልጿል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ.ር) መግለጫ ጠቅሶ የጻፈው ብሉምበርግ ደግሞ ቀጣናዊ ውጥረቶች በተባባሱበት በዚህ ወቅት ግዢው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር፣ በቀጣናው ላይ የጋራ ደኅንነትን እና መረጋጋትን ለማረጋገጥ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርላትም አትቷል።

በተመሳሳይ ዘ ሞስኮ ታይምስ ጋዜጣ ባወጣው ጥልቅ ትንታኔ የአራተኛ (4++) ትውልድ ሱ-35 ተዋጊ ጀቶች እና የኤስ-400 መከላከያ ዘዴዎች መታጠቅ የኢትዮጵያን ጥቃት አስቀድሞ የመከላከል እና የመቀልበስ አቅሟን ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግርም አትቷል።

የደኅንነት እና የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኞች የሁለቱን ሀገራት ስምምነት አስመልክቶ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በሰጡት አስተያየት ደግሞ ይህ ታሪካዊ ትጥቅ በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የወታደራዊ ኀይል ሚዛን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀይራል ብለዋል። ለኢትዮጵያ ፍጹም የኾነ የአየር ላይ የበላይነትን የሚያጎናጽፍ መኾኑንም ገልጸዋል።

የመከላከያ እና ስትራቴጂያዊ መረጃዎችን በመተንተን የሚታወቀው ጃንስ የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም በሞስኮ ጅኮቭስኪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የታዩትን እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያረፈባቸውን ተዋጊ ጀቶች ምስል እና ቪዲዮ መሠረት አድርጎ ሀተታውን አቅርቧል።

ዓለም አቀፍ ተቋሙ የተዋጊ ጀት እና የአየር ላይ መከላከያ ዘዴዎች ግዢው የኢትዮጵያን አየር ኀይል ሙሉ በሙሉ ወደ ዘመናዊነት የሚያሸጋግር ነው ብሎታል። ስምምነቱ የፓይለቶች የላቀ ሥልጠናን እና የቴክኒክ ድጋፍን ያካተተ መኾኑ ደግሞ የኢትዮጵያን አየር ኀይል ዘላቂ የቴክኖሎጂ ባለቤት እንደሚያደርገውም ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋሞቹ ጨምረው አብራርተዋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር የፈጸመችው የአየር ኀይል ትጥቆች የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀንን እና የወታደራዊ ሳይንስ ተንታኞችን ትኩረት ስቧል። ለኢትዮጵያ ክፉ ለሚመኙ ጠላቶች ደግሞ ራስ ምታት ኾኗል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_19_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleከኮንፈረንስ ቱሪዝም እስከ ስፖርት ቱሪዝም፤ የባሕር ዳር አዲስ ከፍታ!
Next article“የኢትዮጵያ እና የሩሲያ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የጸና ታሪካዊ ወዳጅነት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)