ወርቃማው መስከረም እና የጸደይ እሼት

7
​”ጨለማው አለፈ፣ ዝናቡ ተመለሰ፣ ፍሬ ለገሰ” እያሉ በደስታ የሚታሰበው የመስከረም ወር፤ ከቀላል አዲስ ዓመትነት ባሻገር ከአባቶች የዘመን ቀመር እና ከኢኮሎጂካል ትስስር ጋር የተዋሐደ ድንቅ ምዕራፍ ነው።
መስከረም ሲጠባ ሰማዩ በብርሃን ይንጸባረቃል፤ ምድርም በአረንጓዴ ልምላሜ ተውባ በቢጫ ሸማ ትቀየጣለች።
የመስክ አበቦች የነገ ተስፋን እያበሰሩ፣ የለመለመው እና የጎመራውን ሰብል በለስላሳ ንፋስ እያነጋገረ ልብ ይስባል። አርሶ አደሮችም የድካማቸውን ፍሬ ለማየት ማሳውን ሲዞሩ በደስታ ይዋጣሉ። በእንቁጣጣሽ ዜማ እና በሆታ ታጅቦ፣ ተፈጥሮ አዲስ እሼት ቋጥራ “እንካችሁ” እያለች ለልጆቿ ታቀርባለች። ይች ወር ተፈጥሮ ተውባ የምትታይበት፣ የአዲስ ዑደት መጀመሪያ የምሥራች የምትነግረን ውብ እና እንቁ ጊዜ ናት።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የባሕል ጥናት መምህር እና ተመራማሪ መስፍን ፈቃዴ (ዶ.ር) እንደገለጹት የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ድንገተኛ ሳይኾን ከተፈጥሮ ኡደት እና ከሀገር በቀል የጠፈር ዕውቀት ጋር ጥልቅ ቁርኝት ያለው ነው ይላሉ።
አዲስ ዓመት የሰዎች ፈጠራ ብቻ ሳይሆን የራሷ ተፈጥሮ የዘመን መለወጫ ግጥምጥሞሽ ማሳያ ነው። በዚህ ወቅት አበቦች ይፈካሉ፣ ወንዞች ይጠራሉ፣ አየሩ ይጸዳል፣ ጎርፉና ጭቃው ይቀንሳል። አበቦች የሚፈኩበት እና የመስቀል ወፍ መታየት የሚጀምሩበት ውብ ወቅት መኾኑንም ይናገራሉ ።
ሌላው ከግብርና ሕይወት ጋር ያለው ትስስር ነው። በተለይም ከአርሶ አደሮች ሕይወት ጋር ያለው ቁርኝትም ሰፊ ነው።
አዲስ ዓመት አርሶ አደሮች የክረምቱን ድካም ጨርሰው፣ የዘር ሂደቱን አጠናቅቀው፣ የምርት ተስፋ የሚያዩበት፣ የእረፍት እና የምስጋና መጀመሪያ ነው። አርሶ አደሮች ከዓመቱን ሙሉ ድካምና ውጣውረድ ወጥተው ምርቱን በጉጉት የሚያዩበትና የመጀመሪያ እሸት የሚቀምሱበት ነው ይላሉ። አርሶ አደሮች የሰማይን ሁኔታ፣ የዝናብ ዑደት እና የምድርን ለምነት በማስተዋል የሚመሩበት የሀገር በቀል ዕውቀት ጎልቶ የሚታየው በዚሁ የዘመን መቀየሪያ ወር ስለመኾኑም ተናግረዋል።
መስፍን ፈቃዴ (ዶ.ር) እንዳብራሩት ሀገር በቀል የሥነ-ክዋክብት ዕውቀት እና ባሕረ ሐሳብ ጋር ያለው ቁርኝት ደግሞ ሌላኛው ነው። የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በፀሐይ እና በጨረቃ ዑደት ላይ የተመሠረተ እና በሳይንሳዊ የስነ-ክዋክብት ስሌት የተደገፈ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
መስከረም የተፈጥሮ ጸጋ፣ የዘመን ሽግግር እና አዲስ ተስፋ ተዋሕደው የሚታዩበት የሐሴት ወር ነው።
#አሚኮ #አዲስ ዓመት# መስከረም#Ethiopia
በሥራውድንቅ ደሳለው
Previous articleየኢትዮጵያ የዘመን ሳይንስ!
Next articleየኢትዮጵያ የዘመን ሳይንስ!