💧 የባዕዳንን ሴል ያጠበ የኢትዮጵያውያን ላብ – የጽናት ጉዞ በሕዳሴ ሲገለጥ🌅

8

 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጫ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም። ተስፋን ከቁጭት፣ ጽናትን ከፈተና ጋር አዋህዶ የተገነባ የሥነ ልቦና ልዕልና ማሳያ ጭምር እንጂ።

የግንባታው የጉዞ ምዕራፍ ከመነሻው ጀምሮ አልጋ በአልጋ አልነበረም። እጅግ ውስብስብ የኾኑ የጂኦ-ፖለቲካዊ አሻጥሮችን፣ የውጭ ኃይሎችን ያልተቋረጠ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ ጫና፣ የውስጥ ፖለቲካዊ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን በጀርባው አዝሎ የተጓዘ እንጂ።

ኀያላን ሀገራት እና የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በፈጠሩት ዘርፈ ብዙ ጫና ኢትዮጵያ እንድትንበረከክ እና ፕሮጀክቱን እንድታቆም ከፍተኛ ጫና ተደርጎባታል። የሥነ ልቦና፣ የዲፕሎማሲ እና የኢንፎርሜሽን ጦርነቱ ከጫናዎቹ መካከል ፈታኞቹ ናቸው። ማዕበሉ የኢትዮጵያውያንን የዓላማ ጽናት በዓለም አደባባይ አጸናው እንጂ ሊያቆመው ግን አልቻለም።

የፈተናው ዋነኛ ምንጭ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት (ግብፅ እና ሱዳን) አግላይ በኾኑት የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ላይ ተመሥርተው የሚያነሱት ማለቂያ የሌለው ተቃውሞ ስለመኾኑ ስለአባት ማናየ “የዓባይ ፖለቲካ እና የባዕዳን ተልዕኮ” መጽሐፍ ላይ አስፍሮታል። የእነዚህ ሀገራት ትክክለኛው ስጋት የውኃ እጥረት ሳይኾን ኢትዮጵያ ኅይል አመንጭታ እንዳትበለጽግ እና ከድህነት እንዳትወጣ የማድረግ ፍላጎት እንደኾነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናግረዋል።

በኢኮኖሚውም ረገድ ፕሮጀክቱ ሲታሰብ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት እና ሌሎችም ምዕራባውያን አበዳሪ ተቋማት በከፍተኛ የጫና ዘመቻ ምክንያት ለግድቡ ግንባታ አንዳችም ብድር ወይም እርዳታ አልሰጡም። ይህ የፋይናንስ ማዕቀብ ግን ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ በመቆም ተግዳሮቶቹን ሁሉ ወደ ዓላማ ጽናት እንዲቀይሩ ገፋፍቷቸዋል። ዜጎች በላብ፣ በደም እና በገንዘባቸው የገዛ ፕሮጀክታቸውን መገንባት ችለዋል።

የውጭ ጫናውን በሕዝብ ጽናት የማሸነፍ ድል የኢትዮጵያውያንን የውስጥ አንድነት ከማጠናከሩም በላይ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም የራስን ሉዓላዊ መብት በድፍረት የማስከበር ደማቅ ታሪክ እና በራስ የመተማመን ሕያው ምስክር ነው።

በግድቡ ምረቃ ላይ ተገኝተው የነበሩት የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሊ ፕሮጀክቱ “ጥቁር ሕዝቦች በራሳቸው አቅም ትልልቅ ተአምራትን መሥራት እንደሚችሉ ያሳዩበት የታሪክ ምዕራፍ በኢትዮጵያ ዕውን ኾኗል” በማለት የኢትዮጵያውያንን ጽናት መስክረዋል።

በወቅቱ አናዶሉ የዜና ወኪል ኢትዮጵያውያን የዓባይ ወንዝን ገድበው ለሀገራቸው ልማት ለማዋል ለዓመታት ደክመዋል ብሏል። ግድቡም ለግብጽ እና ለሱዳን ጭምር የጋራ ዕድል ይዞ መምጣቱን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን በእውነታ እና በምክንያት ላይ ተመስርተው እንዲያደርጉ ጽፏል።

ለዓመታ የዘለቀው የጽናት እና የአይበገሬነት ተምሳሌት ዛሬ ፍሬ አፍርቷል። 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኀይል የማመንጨት አቅም ላይ ደርሷል። ይህ ታላቅ ስኬት የሀገር ውስጥ የኅይል ችግርን ከማቃለል ባለፈ ከኅይል ሽያጭ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንዲጠበቅበት ኾኗል።

ግድቡ በኢትዮጵያ ትልቁን ሰው ሠራሽ የንጋት ሐይቅን በመፍጠር ለዓሣ ሀብት ልማት ትልቅ አቅም ኾኗል፤ በሐይቁ ላይ የተፈጠሩት ከ78 በላይ ደሴቶች፣ የውኃው አካል እና በዙሪያው ያለው ተፈጥሮ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ አዲስ እና ተጨማሪ ሞተር በመኾን ብቅ ብሏል።

ሕዳሴ ግድብ የሲሚንቶ፣ የውኃ እና የብረት ክምችት ብቻ አይደለም። ይልቁኑ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ከተያያዙ እና በአንድ ሀገራዊ ራዕይ ላይ ከጸኑ ማናቸውንም ምድራዊ ኅይል ተቋቁመው ተዓምር መሥራት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጠ ነው።

ግድቡ በችግሮች ውስጥ ተወልዶ፣ በፈተናዎች ታሽቶ፣ በጽናት ያደገ የትውልድ አሻራ ነው። ጳጉሜን ሦሥት ደግሞ ይህንን የትላንት አኩሪ ትግል በማሰብ፣ የዛሬውን ድል በማክበር እና የነገውን ብሩህ የብልጽግና ተስፋ በላቀ ጽናት ለመቀበል የቃል ኪዳን ቀን ኾና ትታሰባለች።

#AMECO #GERD #Megaproject #ItsMyDam #EthiopianResilience #Ethiopia🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጳጉሜን_03_2018_ዓ_ም

✍️ በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleሩፋኤል – የአማራ እና ኦሮሞ ሕዝቦች የአብሮነት ምስክር በዓባይ ወንዝ!