🌟 የብርሃን እና የልምላሜ ዑደት – ከቡሄ እስከ ግሸን 🌿

18

🌟 የብርሃን እና የልምላሜ ዑደት – ከቡሄ እስከ ግሸን 🌿

የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ ዋዜማ እና መባቻ ከክረምት ማብቂያ እስከ ጸደይ መግቢያ ያለው ጊዜ፤ ተፈጥሮ ልምላሜን የምትለብስበት ብቻ ሳይኾን የሰው ልጅም ነፍስ በሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት የምትታደስበት ልዩ ወቅት ነው። ከነሐሴ 13 ጀምሮ እስከ መስከረም 21 ድረስ ያለው የጊዜ ሰሌዳ እንደ አንድ ውብ ኪናዊ ድርሰት ተሰናስሎ የሚነበብ፣ ቀለም እና ለዛ ያለው መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ጉዞ ነው።

🔥 የብርሃኑ ብልጭታ – ደብረ ታቦርን በደብረታቦር (ቡሄ)

ከከባድ የክረምት ዝናብ እና ጭጋግ በኋላ የመጀመሪያው የብርሃን ብልጭታ የሚታየው በነሐሴ 13 የቡሄ በዓል ዕለት ነው ተብሎ ይታመናል። ለዚህም ነው “ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት…” በሚል በሀገሬው ስንኝ ቋጠሮ የሚነገረው።

ጅራፍ እና ሆያ ሆዬ፡- ጅራፉ ሲጮህ የክረምቱን ነጎድጓድ ይወክላል። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ “ክረምት አለፈ፣ ብርሃን መጣ” የሚል የማብሰሪያ ደወል ነው። የልጆች የሆያ ሆዬ ዜማ ጭጋጉን ገልጦ የሚመጣውን የተስፋ ድምጽ ያሰማል።

ሙልሙል ዳቦ እና ችቦ:-

እናቶች የሚጋግሩት ሙልሙል ዳቦ የፍቅር፣ የመተሳሰብ እና የበረከት ተምሳሌት ተደርጎ ይቆጠራል። ምሽት የሚለኮሰው ችቦ ደግሞ ታቦር ተራራ ላይ የታየውን መለኮታዊ ብርሃን በምድር ላይ የሚያንጸባርቅ ባሕላዊ ማሳያ ነው።

💃 የልምላሜ እና የውበት ዜማ – አሸንድዬ፣ ሻደይ እና ሶለል የጾመ ፍልሰታን ማብቃት ተከትሎ ከነሐሴ 16 ጀምሮ በልዩ ድምቀት ይከበራሉ። ይህ ክዋኔ የሴትነት ጥንካሬ፣ ውበት እና ነጻነት መገለጫ ነው። ልጃገረዶች ሐመልማል በወገባቸው አስረው፣ ጸጉራቸውን ተሠርተው፣ በልዩ ባሕላዊ አልባሳት አጊጠው ሲጫወቱ ምድር ከለበሰችው አረንጓዴ ልምላሜ ጋር ይዋሃዳሉ። የከበሮው ምት እና የእግሮቻቸው አረማመድ የአንድነት እና የኅብረት ዜማ ይፈጥራል።

🌾 የመዓዛ እና የንጽህና ዝግጅት – እንግጫ እና ከሴ

ወደ አዲሱ ዓመት መግቢያ ላይ በተለይም በጎጃም እና አካባቢው የሚዘወተር ባሕላዊ ክዋኔ ነው። ይህም ሥነ ሥርዓት ሌላው የተስፋ እና የሽግግር ወቅት ተደርጎ ይቆጠራል።

ልጃገረዶች ማለዳ ተነስተው በዝማሬ እና በእልልታ ሜዳውን ሞልተው እንግጫ ሲነቅሉ የክረምቱን ጭቃ እና ድባቴ ነቅለው በመጣል አዲሱን የብርሃን ዘመን በንጹህ መንፈስ የመቀበል ህያው ምሳሌ ነው። ነጫጭ አበባ ያለውን እንግጫ ለእናቶቻቸው ሲያበረክቱ፣ “እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ” የሚል የፍቅር እና የበረከት መልዕክት አለው። ከዚህ ጎን ለጎን የሚታጨደው መዓዛማው ከሴ ቤቱን ሲያውደው፣ የክረምቱን ሻጋታ ጠረን በአዲስ የጸደይ ጠረን ይተካዋል፤ ቤቱም ኾነ ነፍስ በአዲስ ተስፋ ይታደሳሉ።

🌼 የሽግግር ድልድይ፡-

ጳጉሜን እና እንቁጣጣሽ የጳጉሜን እና የመስከረም 1 የዘመን መለወጫ (እንቁጣጣሽ) የሽግግር ድልድዮች ናቸው። በጳጉሜን ወንዝ መውረድ ያለፈውን ዘመን ኃጢአት እና ቆሻሻ አጥቦ አዲሱን ዘመን በንጽህና ለመቀበል የሚደረግ መንፈሳዊ ዝግጅት ነው። መስከረም ወር ላይ ምድር በአደይ አበባ ስትንቆጠቆጥ የሰው ልጅም በአዲስ ተስፋ ይሞላል። ልጃገረዶች “አበባ አየሁሽ…” እያሉ ሲዘፍኑ ተፈጥሮ ልሡ በሰው ልጆች አንደበት ስትዘምር ይሰማል።

✝️ የዕውቀት እና የብርሃን ድል – የመስቀል ደመራ
ዘመኑ ብሩህ ኾኖ በገባ በመስከረም 16 እና 17 የመስቀል ደመራ በዓል ይከበራል። ደመራው ሲለኮስ ወደ ሰማይ የሚወጣው ጢስ የጸሎት፣ የእምነት እና የፍለጋ ጉዞ ምሳሌ ነው። የተሠበሠበው እንጨት ወደ ብርሃን (እሳት) ሲቀየር ድንቁርና በዕውቀት፣ ጨለማም በብርሃን የመሸነፉ ምልክት ነው።

በማግሥቱ የሚከበረው የመስቀል በዓል በመስቀል አደባባይ በሚቀርቡት ያሬዳዊ ዝማሬዎች፣ በካህናቱ የኅብረት ውዝዋዜ እና በአማኞች ነጭ አልባሳት መንፈሳዊነትን ከባሕላዊ ማንነት ጋር የሚያዋህድ ህያው ሁነት ነው።

⛰️ የመንፈስ ዕረፍት – ግሸን ደብረ ከርቤ

ይህ የብርሃን እና የደስታ ጉዞ በመስከረም 21 በግሸን ደብረ ከርቤ ጥልቅ መንፈሳዊ ስሜት እና ጸጥታ ውስጥ ይቋጫል። ግሸን ተራራ ላይ ለመድረስ የሚደረገው አድካሚ ጉዞ የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚያደርገውን የሕይወት ውጣ ውረድ ይወክላል ተብሎ ይታሰባል። ተራራውን ወጥቶ መሳለም ከኃጢአት ሸክም የመገላገል፣ የነፍስ ዕረፍት የማግኘት ተምሳሌት ተደርጎ ይቆጠራል። በዚህ ቀን ግሸን በነጭ ለባሾች ስትጥለቀለቅ ምድር ከሰማይ ጋር የተገናኘች፣ የሰው ልጅ ከመልአክት ጋር ያበረበት አምሳል ኾና ትታያለች።

ከቡሄ እስከ ግሸን ማርያም ያሉት የቀናት ጉዞ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከተስፋ ወደ ዕውን፣ ከፍለጋ ወደ ግኝት እና በመጨረሻም ወደ ዕረፍት የሚደረግ የሰው ልጅ ጥልቅ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ ጉዞ ውብ መግለጫም ነው።

#አሚኮ #አማራ_ክልል_ባህልና_ቱሪዝም #ከቡሄ_እስከ_ግሸን #የኢትዮጵያ_ባሕል

#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_04_2018_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየሃሳብ ብዘኃነት ለሀገራዊ ምክክር ግብዓት ወይስ ፈተና?
Next articleየኢትዮጵያ የ5 ሚሊዮን ኮደሮችን ቁጥር ወደ 7 ሚሊዮን የማድረስ ጉዞ✨