
#ባሕር_ዳር ሰኔ 27/2018 ዓ.ም የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሚዲያ እና ኮሙዩኒኬሽን መሪዎች እና ባለሙያዎች ጋር የትምህርት ሚዲያ ፎርም ውይይት እያካሄደ ነው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ጥላሁን ወርቅነህ ትምህርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት እና ብልጽግና ቁልፍ መሳሪያ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በሀገር ደረጃ እና በክልሉ ዘመናዊ እየተባለ የሚጠራው ትምህርት የረጅም ጊዜ ታሪክ ቢኖረውም አሁንም ከጥራት፣ ከፍትሐዊነት እና ከተሳትፎ አኳያ በርካታ ጉድለቶች አሉበት ነው ያሉት።
ይህንንም በዘላቂነት ለመፍታት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ ፖሊሲ እና ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት የትምህርት መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፤ መምህራን እና ተማሪዎች ለቀውስ ተዳርገዋል ነው ያሉት።
ይህንን ፈታኝ ሁኔታ በጋራ ለመቀየር በ2018 በጀት ዓመት በኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ የትውልድ ንቅናቄ አቅም ማጠናከር፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የቅድመ አንደኛ ማስፋፊያ፣ የልዩ ተሰጥኦ ማዕከላት ላይ ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።
እንደ ፊንላንድ፣ ሲንጋፖር እና ደቡብ ኮሪያ ያሉ በዓለም ላይ ስኬታማ የትምህርት ሥርዓት የገነቡ ሀገራት ሚዲያን እንደ ዋና የልማት አጋር እንደሚጠቀሙ አንስተዋል፡፡ በአማራ ክልልም በትምህርት ጥራት እና ተሳትፎ ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ሚና ለነበራቸው የሚዲያ ተቋማት እና ባለሙያዎች ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
መጭው ጊዜ በጋራ ሠርቶ የትምህርት ግቦችን የማሳኪያ እንዲኾንም አሳስበዋል።
#በትምህርት_ለትውልድ #የአማራ_ትምህርት #ትምህርት_ለንቅናቄ #Ethiopia
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
