በፍኖተ ሰላም ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ ነው።

7

 

ፍኖተ ሰላም: ግንቦት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በፍኖተ ሰላም ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሽፈራው በቄ በልማቱ መጀመር መደሰታቸውን ገልጸው አሁን ያለው የሰላም ሁኔታ መሻሻል ለሥራው መሳካት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በኮሪደር ልማቱ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችም ፕሮጀክቱ ከስደት እንደታደጋቸው እና ራሳቸውን በኢኮኖሚ ለማብቃት እንዳገዛቸው ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሀንዲስ አስቻለው አይናለም የግራና ቀኝ የውኃ ማፋሰሻ ቦይ ሥራ 98 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸው ግንባታውን እስከ ሰኔ 30 ለማጠናቀቅ ተጨማሪ የሰው ኀይል እና ግብዓት ቀድሞ ማቅረብ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የፍኖተ ሰላም ከተማ የመሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ወርቅነህ ድረስ ጥር/2018 ዓ.ም የተጀመረው እና በአምስት ወራት ለማጠናቀቅ ዕቅድ የተያዘለት የዚህ ፕሮጀክት አሁናዊ አፈጻጸም 13 በመቶ ላይ መኾኑን ጠቁመዋል።

ለግንባታው መጓተትም በጅማሮው ወቅት ያጋጠሙ የግብዓት፣ የሥራ መደራረብ እና የነዳጅ እጥረት ችግሮችን በምክንያትነት አንስተዋል።

የፍኖተሰላም ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጊዜው ደግአረገ እንደገለጹት ለዚሁ የመንገድ ኮሪደር ግንባታ 219 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዟል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ ከዓደባባይ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት ያለውን የሚያካትት ሲኾን ግንባታው በታላላቅ ከተሞች በሚሠራበት የኮሪደር ስታንዳርድ እየተከናወነ ነው። የእግረኛ፣ የብስክሌት እና የአረንጓዴ ስፍራዎችን ያካተተ እንደኾነም ጠቁመዋል።

የኮሪደር ሥራው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የተማዋን ደረጃ ከፍ እንደሚያደርጋት አረጋግጠዋል።

#አሚኮ_ዜና #የኮሪደር_ልማት #ፍኖተ_ሰላም #አማራ_ክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

Previous articleበምርጫው ቀን መሥሪያ ቤቶች ዝግ ኾነው ዜጎች ድምጻቸውን እንደሚሰጡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በያቤሎ ከተማ የተገነባውን የቦረና ባሕል ማዕከል መርቀው ሥራ አሥጀመሩ።