“የታጣቂዎች ትግል ዓላማ የሌለው የግለሰቦች መነገጃ ኾኗል” ፍቅሩ ሙሉየ

10

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

በትምህርት ቤቶች፣ በጤና ተቋማት እና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ውድመት የክልሉን የልማት ጉዞ ወደ ኋላ እየጎተተው ይገኛል። የክልሉን ነዋሪዎችም ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጓል።

በበርካታ አካባቢዎች በተደረጉት ሕዝባዊ ውይይቶች ለዘላቂ ሰላም የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም ሕዝቡ በየመድረኩ እየጠየቀ ነው። ጫካ የገቡ ኀይሎች ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሊመለሱ እንደሚገባም ማኅበረሰቡ እንደየሽምግልና እና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱ እየተማጸነ ነው።

መንግሥትም በተደጋጋሚ ባቀረበው የሰላም ጥሪ መሠረት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን እየተቀበሉ ነው።

በተለይም የሰላምን አማራጭ መርጠው ከጫካ የተመለሱት እንደ ፍቅሩ ሙሉየ ያሉ ወጣቶች ምስክርነት የትግሉን መራራ ዕውነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ፍቅሩ ሙሉየ እንደተናገረው አሁን ያለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ክልሉን በኢኮኖሚ እያደቀቀው እና በድህነት እንዲኖር እያደረገው ነው ብሏል።

“እኔም በተሳሳተ መንገድ ወደ ትግል ገብቸ ነበር” የሚለው ፍቅሩ አሁን ግን ያለው እንቅስቃሴ ለሕዝብ የማይበጅ በመኾኑ የሰላም አማራጭን መቀበልን መርጫለሁ ብሏል።

ሕዝብ በስቃይ ሊኖር እንደማይገባውም ይገልጻል። ጦርነት ለማንም አይበጅም፣ በክልሉ ባለው ግጭት ሕዝብ እየተበደለ እና ማኅበራዊ ቀውስም እየተባባሰ መቆየቱን ጠቁሟል። ይህ እንዲቆም እና ሕዝብ እፎይታ እንዲያገኝ ታጣቂዎች በሙሉ ወደሰላም መመለስ አለባቸው ነው ያለው።

“የታጣቂዎች ትግል ለሕዝብ አይጠቅምም፤ ዓላማ የሌለው የግለሰቦች መነገጃ ኾኗል” የሚለው ፍቅሩ ሕዝቡም በታጣቂ ቡድኑ እየተማረረ፣ ጠዋት እህል አምጣ፣ ማታ ብር ክፈል እየተባለ ለስቃይ መዳረጉን አስረድቷል።

በጫካ ያሉት አካላትም መንግሥት የዘረጋውን የሰላም አማራጭ በመቀበል ወደ ሰላም መምጣት እንደሚገባቸው ነው የተናገረው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአርሶ አደሮችን ማዳበሪያ እና የእናቶችን አምቡላንስ መዝረፍ ከኢትዮጵያዊነት እሴት የራቀ ነው።
Next articleበነጻ የንግድ ቀጠና ውስጥ ተሰማርተው ምርቶችን ለገበያ የሚያቀርቡ ባለሃብቶች ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ ተፈቀደ።