
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስማዳ ወረዳ ነዋሪዎች እንዳሉት በሕዝብ ስም የሚነግዱ ታጣቂዎች የማኅበረሰቡን መገልገያ ተቋማት አውድመዋል። የሕዝብ መገልገያ ንብረትን ማውደም ማኅበረሰቡ በድህነት እንዲኖር እና በኢኮኖሚ እንዲዳከም ማድረግ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ የታጣቂዎቹን ድርጊት አውግዘዋል።
የደረሰው ውድመት አገልግሎት ለማግኘት እንድንቸገር አድርጎናል ነው ያሉት።
ለምርታማነት የሚያገለግል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ሳይደርስ በታጣቂ ኀይሉ መዘረፉንም አንስተዋል። ይህም በአርሶ አደሮች ሕይወት ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።
የታጣቂዎችን ግፍ የምንቋቋምበት አቅም የለንም ያሉት ነዋሪዎቹ ሰላምን ለማጽናት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አንስተዋል።
አሁን ላይ በወረዳው አንጻራዊ ሰላም መኖሩንም ተናግረዋል። ሰላም በመንግሥት ጥረት ብቻ አይመጣም ያሉት ነዋሪዎቹ በመደራጀት አካባቢን በንቃት በመጠበቅ ሰላማቸውን እንደሚያጸኑም ጠቁመዋል።
የስማዳ ወረዳ አሥተዳዳሪ እንዳልክ ጥላሁን የጥፋት ኀይሎች በወረዳው በቆዩበት ጊዜ ከ8ሺህ 600 በላይ የአፈር ማዳበሪያን በመዝረፍ ለሕገወጥ ነጋዴዎች መሸጣቸውን ተናግረዋል።
ይህ ተግባር በአርሶ አደሮች ላይ የሥነ ልቦና ጫና ያሳደረ እና በቀጣይ ምርታማ እንዳይኾኑ እንቅፋት የፈጠረ ነው ብለዋል።
አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማቃጠል ንብረቶች መዝረፋቸውን አንስተዋል። በተለይም ስድስት የወላድ እናቶች መገልገያ አምቡላንሶችን መዝረፋቸውንም ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ በጤና ተቋማት የሚገኙ መድኃኒቶችንም መዝረፋቸውን አንስተው ይህም በማኅበረሰቡ የሕክምና አገልግሎት አሠጣጥ ላይ ጫና ማሳደሩን ተናግረዋል።
ታጣቂ ኀይሎች በወረዳው በቆዩበት ወቅት ተቋማትን ከማውደም እና ከመዝረፍ ባሻገር ንጹሐንን በመደብደብ፤ የተለያዩ አጸያፊ ተግባራትን መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
መንግሥት በወሰደው ሕግ የማስከበር ሂደት አማካኝነት አሁን ላይ በወረዳው አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ያነሱት አሥተዳዳሪው ሕዝቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በመኾን የአካባቢውን ሰላም እያስጠበቀ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የታጣቂ ኀይሎችን ግፍ በማስቆም ማኅበረሰቡ ለሰላም መስፈን የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
