
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ መቀያየር በትራንስፖርት ታሪፍ እና በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ ጫና እያሳደረ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት እና ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ተሽከርካሪዎችን ከነዳጅ ወደ ተፈጥሮ ጋዝ እና ወደ ኤሌክትሪክ ኅይል የማሸጋገር ሥራ እየሠራ ነው።
የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የአውቶሞቲቭ ትምህርት ክፍል ኢንስትራክተር እና የትራንስፖርት ቴክኒሽያን ማሠልጠኛ ማዕከል ቡድን መሪ ሙስጠፋ አደም እንደገለጹት ይህ የሙከራ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ በሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ እየኾነ ነው።
ሂደቱም ነባር ሞተሮችን ሳይቀይሩ የጋዝ ሲሊንደር፣ የግፊት መቆጣጠሪያ እና ጋዝ ረጭ በመግጠም የሚከናወን ነው ብለዋል።
ስትራቴጂካዊ እርምጃው ሀገሪቱ ለነዳጅ ግዥ የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚታደግ እንደኾነም ተናግረዋል።
በተለይም ዕድሜ ጠገብ ተሽከርካሪዎች ያላቸው መዋቅር ለዚህ ሽግግር ምቹ በመኾኑ የአገልግሎት ዘመናቸውን ለማራዘም እንደ ትልቅ ዕድል እንደሚታይ ነው የጠቆሙት።
ወደ አማራጭ የኅይል ምንጮች የሚደረገው ጉዞ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር ኢትዮጵያ የያዘችውን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ግብ የሚያፋጥን እና የአየር ብክለትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ ነው።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምንም ዓይነት የጭስ ልቀት የሌላቸው መኾኑ እና የጋዝ አማራጭም ከነዳጅ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ በካይ ጋዞችን የሚለቅ በመኾኑ ለአካባቢ ጥበቃ የላቀ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
ይሁን እንጂ ይህንን የቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤታማ እና ዘላቂ ለማድረግ በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ በኩል ሊታለፉ የማይገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የኀይል መሙያ ጣቢያዎችን በስፋት መገንባት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ማቅረብ እና ቴክኖሎጂውን የሚጠግኑ ባለሙያዎችን ማሠልጠን የሂደቱ ወሳኝ መፍትሔዎች መኾናቸውን ገልጸዋል።
የቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት ሥርዓተ ትምህርታቸውን በማሻሻል ብቁ የሰው ኀይል ማፍራት ላይ ሊያተኩሩ ይገባልም ብለዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጎማ እና ማበረታቻ በማድረግ፤ ሚዲያዎችም ኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ስጋት በመቅረፍ ረገድ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የነዳጅ እጥረትን በዘላቂነት በመፍታት ረገድ የተጀመረው ጉዞ ለሀገር ኢኮኖሚ እና ለተጠቃው ሕዝብ እፎይታን የሚያመጣ ብሩህ ተስፋ እንደኾነም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
