ትንሣኤ ችግሮች ሁሉ እንደሚያልፉ ማሳያ ነው።

7

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለተኝቶ ታካሚዎች እና አስታማሚዎች ማዕድ አጋርተዋል።

ማዕድ የተጋሩ ተኝቶ ታካሚዎች እና አስማሚዎች በዓልን በሆስፒታል ኾኖ ማሳለፍ ከባድ መኾኑን ተናግረዋል።

የተደረገልን የምሣ ግብዣ ጭንቀታችንን እረስተን በዓሉን በደስታ እንድናከብር አድርጎናል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሃም ትንሣኤውን ከተቸገሩት እና ከሕሙማን ጋር አብሮ ማክበር የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሁልጊዜ መልዕክቷ ነው ብለዋል።

ይህንን አስበው በትንሣኤው ማዕድ ያጋሩትን የሥራ ኀላፊዎችም አመስግነዋል።

የፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ዐቢይ ፍሰሐ ሆስፒታሉ በርካታ ሕሙማንን ይዞ ሕክምና እየሰጠ ነው ብለዋል። ሆስፒታሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ አንደኛ በመውጣት መሸለሙንም ጠቅሰዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ በዓላትን ስናከብር በመተባበር፣ በመረዳዳት እና ያለው ለሌለው እየሰጠን መኾን አለበት ነው ያሉት።

ሆስፒታሉ አሁን ላይ ራሱን እያዘመነ የተሻሻለ ሕክምና እየሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ እና የሆስፒታሉ ቦርድ ሰብሳቢ ፍሰሐ ደሳለኝ በዓሉን ስናከብር ለሰላም እየሠራን እና የሌላቸውን እየረዳን መኾን አለበት ብለዋል።

በሆስፒታሉ ተገኝተው ከሕሙማን ጋር በማክበራቸውም ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በዓሉ የአሸናፊነት በዓል ነው ያሉት አቶ ፍሰሐ የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮች በአንድነት ከቆምን ማለፍ እንደምንችል የትንሣኤ በዓል ማሳያ ነው ብለዋል።

በዓሉ የመተሳሰብ፣ የአንድነት እና የመረዳዳት እንዲኾንም ተመኝተዋል።

ዘጋቢ ፦አድኖ ማርቆስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየበጎ አድራጎት ሥራ የሁል ጊዜ ተግባር መኾን አለበት።