
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እንደተናገረ ተነሥቷል፤ በኃይሉ ሞትን ድል ነሥቷል፤ ከሙታን ተለይቷል፤ የዘመናት ቁራኛንም ፈትቷል፤ በድቅድቅ ጨለማ የተጣሉ ነፍሳትንም አንሥቷል።
መቃብር ሳይከፈትለት፤ መግነዝ ሳይፈታለት፣ የመቃብር ጠባቂዎች ሳያዩት፤ ጠባቂዎችም ሳይዙት በፈቃዱ እንደሞተ በኃይሉ ተነሥቷል።
ፈጣሪዋ ሲሰቀል የጨለመች ዓለም በብርሃን ተመላች፤ በትንሣኤው ተደሰተች፤ ሲኦል ባዶዋን ቀረች፤ ነፍሳትን ተነጠቀች፤ ጨለማ ካባዋ የነበረች ሲኦል በጌታ ብርሃን ተጥለቀለቀች፤ ነፍሳትንም አሳልፋ ሰጠች።
እርሱ ተነሥቷልና በስቅለቱ ያለቀሱት ስቀዋል፤ በስቅለቱ የተደሰቱት ደንግጠዋል፤ አዝነዋል፤ አብዝተውም ተጨንቀዋል። ሞት የሚያስቀረው፤ መቃብር የሚያስረው መስሏቸው ነበርና መቃብር ክፈቱልኝ፣ መግነዜንም ፍቱልኝ ሳይል ተነሥቶ ለዓለም አብርቷልና የሰቀሉት ተሸብረዋል፤ የወጉት ተቅበዝብዘዋል።
በስቀለቱ ያለቀሱት ግን ለደስታ ተነስተዋል፤ ለምስጋና ተሰብስበዋል፤ ሰማይ እና ምድር በደስታ ተመልተዋል፤ ሰው እና መላዕክት ለምስጋና ቆመዋል። በስቅለቱ በእናትነት አንጀት ያለቀሰችው፤ አብዝታም ያነባችው እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከፀሕይ ብርሃን ልቃ በደስታ በርታለች፤ በልጇ መነሳት ሀሴትን አድርጋለች።
ላሐ ማርያም ወሰቆቃዎ ድንግል በተሰኘው መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ ከመቃብሩ አጠገብ ስታለቀስ ተገለጠላት እና እናቴ ድንግል ማርያም ሆይ ለዓለም ያደረግሁት ማዳኔን እይ፤ አሁን በፍስሐ ሕይወት ደስ አሰኝሻለሁ።
እናቴ ሆይ ትንሣኤ እና ሕይወት እኔ ነኝ። በቀራንዮ ደሜ የፈሰሰው ልጅሽ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ። ከሀዘንሽ የማረጋጋሽ ልጅሽ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ።
ስለእኔ እንባሽን እያፈሰስሽ ያለቀስሽልኝ እነኾ ሕያው ነኝ እና ከሞት የተነሣሁ ልጅሽ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ። ከሁሉ አስቀድሞ ደስ ያሰኘሁሽ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ እኔ ነኝ። እናቴ ሆይ ማንም ምን ስጋዬን አልነካም። በራሴም ሥልጣን በአባቴም ፈቃድ ተነሣሁ እንጂ አላት። ድንግልም ይሄንን በሰማች ጊዜ በሥጋ በነፍስ የሚያረጋጋ ፍጹም የደስታ መንፈስን ተመልታ ከልቅሶ እና ከዘሀን ተጽናናች ተብሎ ተጽፏል።
በስቅላት ያነባችው እመቤታችን በትንሣኤ ሀሴትን አደረገች፤ ልጇም ሀዘኗን በደስታ ሻረላት፤ በሀዘን የተቃጠለች አንጀቷን በፍስሐ አለመለማት።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ የአራቱ ጉባዔያት መምህር ርእሰ ሊቃውንት አባ ገብረ ኪዳን ግርማ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሳፍሮ፤ የሞትን ራስ ሰብሮ ተነሣ፤ በዚህም ሕይወታችን ተመሠረተ፤ የትንሣኤ ልጆች ለመኾን በቃን፣ የመንግሥተ ሰማያት ባለርእስት ኾንን ይላሉ።
ትንሣኤ የሰው ልጅ የማንነቱ ትርጉም ነው፤ ጌታ ባይነሣ ኖሮ ሰው ሰውነቱ ትርጉም የለሽ በኾነ ነበር፤ እንደተነሳ የሰው ልጅ ከበረ፤ የሰው ባህሪ በሞት ላይ ሠለጠነ ነው የሚሉት።
ሊቁ ሲናገሩ እርሱ ፋሲካችን ነው፤ ፋሲካ ማለት መሻገር፣ ማለፍ ማለት ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ያሻገረን፤ ከሲኦል ያወጣን እውነተኛው ፋሲካችን ነው፤ የፋሲካ በዓልም የክርስቶስ በዓል ነው ይላሉ።
ክርስቶስ ያዳነን ምህረት ከሌለው ከዲያቢሎስ፤ ከዘላለማዊ እሳት ነው፤ የእርሱ ደም ዓለም ሁሉ የተቀደሰበት ነው፤ ፋሲካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታላቅ ኃይል ተነሣ፤ አብረነው እንነሣ ዘንድ ትንሣዔውን በየዓመቱ እናከብረዋለን ነው የሚሉት።
እርሱ ተነሥቷልና ስንፍና ያለበት ከስንፍናው፤ ወድቀት ያለበት ከውድቀቱ መነሣት አለበት፤ እርሱ ግን ሁልጊዜ ሕያው ነው ይላሉ።
እርሱ በተሰቀለ ጊዜ ምድር ተነዋወጠች፤ ፈራችው፤ ሰማይም ኃይሉን መሰከረች፤ ጨረቃ ብርሃኗን ጋረደች፤ በሥልጣኑም ነፍሱን ከስጋው ለዬ፤ በመቃብር አድሮም ኃይሉን ይገልጥ ነበር ይላሉ ሊቁ።
እነሣለሁ ብሏልና በመቃብሩ ላይ ጊዜ ታላቅ ድንጋይ ዘጉበት፤ ጠባቂ ወታደሮችም አቆሙበት፤ እርሱ ግን የድንጋዩ ከባድነት አላስቆመውም፤ ጠባቂዎችም አልያዙትም፤ በሥልጣኑ ተነሣ እንጂ። እርሱ ኃይል ነውና ሁሉንም አሸንፎ ተነሣ። እርሱን ሞት ይዞ ሊያስቀረው አይችልም።
በታተመ ማሕጸን ተጸነሰ፤ በታተመ ማሕጸን ተወለደ፤ በታተመ መቃብርም ተነሣ፤ በታታመ በርም ገባ፤ ከእርሱ ውጭ ማንንም ሊያደርገው የማይችለውን አድርጎ ኃይሉን ገለጠ፤ የሰውን ልጅም አዳነ ይላሉ።
ክርስቲያኖች በኃይሉ የተነሣውን የጌታቸውን ትንሣኤ ያከብሩታል፤ በትንሣኤው ትንሣኤውን የሰጣቸውን አምላካቸውን ያመሰግኑታል።
እነኾ ያቺ ቀን ዛሬ ናትና ትንሣኤውን እያከበሩት፤ ምስጋና እያቀረቡለት፤ በትንሣኤውም ደስ እየተሰኙበት ነው።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
