“በገዛ ሥልጣኑ ሞትን ድል ነሳ”

6

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል ትንሣኤ ቀዳሚ ነው።

ትንሣኤ በግዕዝ ተንሥኦ ወይም ተነሳ ከሚለው ቃል የተገኘ ሲኾን መነሳት ማለት እንደኾነ የተናገሩት በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል መምህር ዮሴፍ ዳኜ ናቸው።

በትንሣኤ ነፍስ እና ስጋ ተለያይተው ከቆዩ በኋላ ዳግመኛ የተዋሃዱበት ነው ብለዋል።

ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ ለዘላዕለም ሕያው መኾንን ያሳየበት እንደኾነ ነው የገለጹት። ከሙታን በመነሳት ለሰው ልጅ ተስፋን ያበሰረበት መኾኑንም ተናግረዋል።

በዕለቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን እና ዲያቢሎስን ድል አድርጎ የተነሳበት፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገሩበት ታላቅ የደስታ በዓል ነውም ብለዋል መምህሩ።

ትንሣኤ፦
👉 ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፤
👉 ከኃጥያት ወደ ጽድቅ፤
👉 ከውርደት ወደ ክብር፤
👉 ከሰይጣን የባርነት ቀንበር ወደ ዘላዕለማዊ ነጻነት፤
👉 ከጎሰቆለ ሕይወት ወደ አዲስ ሕይወት የተለወጠበት ታላቅ መንፈሳዊ የነጻነት በዓል እንደኾነም መምህር ዮሴፍ አስረድተዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሳ እንደተናገረው ሁሉ ከሞት መቃብር ላይ በሦስተኛው ቀን፤ በዕለተ እሁድ ብርሃነ መለኮቱን ገልጦ፤ “በገዛ ሥልጣኑ እና ኃይሉ ድል አድርጎ ተነስቷል” ነው ያሉት።

የሰው ልጅ በምጽዓት ጊዜ ነፍስን እንደሚዋሐድም አሳይቷል ነው ያሉት። ያን ጊዜ ምድር በኃጥያት ቆሽሻ የነበረችው በክርስቶስ ደም ታጥባ እና ነጽታ ደስ እንደተሰኘች ሁሉ ፋሲካ ደስታ ነው ብለዋል።

ትንሣኤ የምስራች የታወጀበት ዕለት እንደኾነ ነው የገለጹት። ምዕመናንም የቤተ ክርስቲያኑ ሥርዓት ሲጠናቀቅ ወደየቤታቸው ይሄዳሉ፤ በዓሉንም በደስታ እና በአብሮነት ያሳልፋሉ ብለዋል።

በታላቁ የትንሣኤ በዓል ምዕመኑ የነበረውን መልካም እና መንፈሳዊ ተግባር ማስቀጠል እንዳለበትም መክረዋል።

የመረዳዳት እሴትን በማጎልበት፤ የተቸገሩ እና አቅመ ደካሞችን በማሰብ አብሮ በጋራ በዓሉን ማሳለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) ማዕድ አጋሩ።
Next articleትንሣኤ የወደቁት የተነሱበት እና ደካሞች የተደገፉበት ዕለት ነው።