“ትንሣኤያችንንም በትንሣኤው አበሰረ” ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

13

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት በሙሉ በቤዛዊ መሥዋዕትነቱ ከሞተ ኃጢዓት ታድጎ የትንሣኤ ሙታንን በር ለከፈተልን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሣኤ እንኳን በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ ብለዋል።

ጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰብዓዊ ክዋኔው ሰው ቢኾንም በመለኮታዊ ክዋኔው የአብና የመንፈስ ቅዱስ ቃል ወይም ወልደ እግዚአብሔር ነው፤ በመኾኑም በሰብዓዊ ክዋኔው መዋች ሲኾን በመለኮታዊ ክዋኔው ተነሽ እና አንሺ ነው፤ ከዚህ አንጻር ሥግው ቃል ሁለቱንም ተግባራት በአንድ አካል እና ክዋኔ የመፈጸም ሥልጣን አለው ነው ያሉት።

ይህም በመኾኑ ራሴን የማኖር እና የማንሣት ሥልጣን አለኝ በማለት እውነታውን እና ምንነቱን አሳየ ብለዋል።
የጌታችን ሞት እና ትንሣኤ ድንገተኛ እና የግድ ሳይኾን ታውቆ ያደረና የውድ እንደኾነ ከዚህ እውነታ እንረዳለን ነው ያሉት።

የሰውን ምልዓተ ኃጢዓት ሙሉ በሙሉ ሰርዞ ሰውን ከሞት ቅጣት ነጻ ለማውጣት ብቃት ያለው ቤዛዊ መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነበረበት፤ ይሁን እንጂ ለዚህ ዓይነቱ ቤዛዊ መሥዋዕት ብቁ የሆነ ከፍጡራን ወገን ስላልተገኘ ራሱ መሥዋዕት፣ ራሱ መሥዋዕት አቅራቢ ሊቀ ካህናት፣ ራሱ ተወካፌ መሥዋዕት አምላክ ኾኖ የቤዛነታችንን መሥዋዕት ራሱ በራሱ ለራሱ አቀረበ ብለዋል።

በቤዛዊ መሥዋዕትም እኛን ከሞት ቅጣት ነጻ አደረገን፤ ትንሣኤያችንንም በትንሣኤው አበሰረ፤ በክርስትና ሃይማኖት የሚገኝ ፍጹም ድኅነት እና ነጻነት በዚህ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ የተመሠረተ ነው።

ጌታችን በትንሣኤው ትንሣኤያችንን ሲያበስረን የትንሣኤ ሰዎች ኾነን በመንፈስና በሞራል በማደግ ብርሃናተ ዓለም ልንኾን እንጂ እንደገና የጨለማው ኃይል መሳሪያዎች ልንኾን አይደለም ብለዋል። የሞቱና የትንሣኤው ምስጢር በንጹሁ ኅሊናችን ካስተዋልነው ውስጣችን እሱን ለመቀበል የሚያዳግተው አይደለም ነው ያሉት።

በትንሣኤው አምነን ትንሣኤያችንን እየተጠባበቅን የምንገኝ ሕዝበ ክርስቲያን በቅን አስተሳሰብ፣ በርቱዕ አእምሮ እና በኃይለ ሃይማኖት እየታገዝን ጨለማውን ዓለም ወደብርሃን ለመለወጥ መጣርና መትጋት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የጨለማው ዓለም መንፈስ ሊያጠፋ ካልኾነ በቀር እንደማይጠቅም የታወቀ መኾኑን ገልጸዋል። ዓለም በጨለማ ተውጦ ሲተረማመስ የሚታየው ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ምርጫው ስላደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

የትንሣኤ በዓላችንን ስናከብር ዓለም በክፋቱ ያጨለመባቸውን ወገኖች ጦማችው እንዳይውሉ ካለን ከፍለን የተራቡትን በማብላት፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የታረዙትን በማልበስ እና የዕለቱ ደስታ ተካፋይ እንዲኾኑ በማድረግ መኾን አለበት ብለዋል።

መልካም የትንሣኤ በዓል እንዲኾንም ተመኝተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።