
ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለትንሣኤ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። የመልእክቱ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
እንኳን ለበዓለ ትንሳዔው አደረሳችሁ!
የትንሳዔ በዓል የነጻነትና የምስጋና በዓል ነው። በትንሣኤው ሞት የተሸነፈበት፤ አዲስ ሕይወት እና ደስታ የተገኘበት ነው።
ከትንሣኤው ትልቅ ጸጋ ተገኝቷል፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገር እንደሚቻል ያስረዳናል። መዳን የታየበት ተስፋ የተገለጠበት፤ ቂም የተሻረበት ፍጹም ሰላምና ታላቅ ፍቅር የተሰጠበት ነው።
በትንሣኤው ሞት የተሸነፈው በይቅርታ እና በትህትና ነው። ለሰው ልጅ ደህንነት ሲል ጽኑ ግፍና በደልን በፅናት ሽሮ አዳምና ዘሩን ከሞት ወደ ሕይወት ቀይሯል። የትንሣኤው ዓላማም ለሕይወት ነው።
ከትንሣኤ ፈተናን ወደ ድል መቀየር እንደምንችል እንረዳለን። ኢትዮጵያውያን የምንፈልገውም ሰላምና ልማት፤ አንድነትና አብሮነትን ነው። ሰላምና ልማት የሚረጋገጠው ደግሞ በጋራ ጥረታችን ልክ ነው።
ከትብብር እና አንድነት ውጭ በልዩነት እና ጥላቻ የሚገኝ ትርፍ አይኖርም። ዛሬም ቂምን በፍቅር፤ በደልን በይቅርታ በመሻር ለሀገራችን ልማት፤ ሰላምና አንድነት በጋራ መቆም ይኖርብናል።
የትንሣኤ በዓልም የእርቅ፣ የሰላም እና የአንድነት ቀን ነው። ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወንበት ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊ እሴቶች እና የአንድነታችን መገለጫ፤ የአብሮነት እና የመተሳሰብ ባሕላችን ማሳያ ጭምር ነው።
ስለሆነም በዓሉን ስናከበር የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ አንድነታችን በማጠናከር፣ ለልማት በመትጋት እና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ በጋራ በመሥራት ሊሆን ይገባል።
መልካም በዓል !!
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
