“ብልጽግና ፓርቲ በችግር ላይ ያሉትን የማኅበረሰብ ክፍሎች እየደገፈ በአብሮነት የሚዘልቅ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ

20

 

ባሕር ዳር፡ ሚያዚያ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በባሕር ዳር ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ያስገነባቸውን ዘመናዊ ቤቶች አጠናቅቆ ለተጠቃሚዎች አስረክቧል።

በመርሐ ግብሩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ብልጽግና ለሁለንተናዊ ልማት የሚተጋ ፓርቲ ነው ብለዋል።

ፓርቲው ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ ሥራውን በተግባር እያሳየ መኾኑን ገልጸዋል። እንደ ሀገር የማይነኩ የሚመስሉ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክትን ያሳካ መኾኑንም ተናግረዋል።

ለዘመናዊ ከተሜነትም ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል። ለአብነትም የባሕር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የመሠረተ ልማት ሥራዎችን አንስተዋል።

ብልጽግና ሰው ተኮር ፖርቲ ነው ያሉት ኀላፊው የቤት ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል። በችግር ላይ ያሉትን የማኅበረሰብ ክፍሎችም እየደገፈ በአብሮነት የሚዘልቅ መኾኑንም አመላክተዋል።

ፓርቲው ችግሮችን እየተሻገረ በከተማም ኾነ በገጠር ሰፊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል፤ በቀጣይም ሰፊ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

ባሕር ዳር ከተማ ከዚህ በላይ የበለጠ እንድትለማ፣ ኢንዱስትሪዎች እንዲበረከቱ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። እነዚህን ቤቶች ለአብነት ሠርቶ አሳየ እንጂ በስፋት የሚቀጥል መኾኑንም አመላክተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ባሕር ዳር በልማት ግስጋሴ ላይ ናት ብለዋል። የመጡ ልማቶች ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የትጋት ውጤቶች መኾናቸውን ተናግረዋል።

የሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ በመደመር መንግሥት እሳቤ የተቃኙ መኾናቸውን ገልጸዋል። ልማቱ ዘላቂ እንዲኾን ሕዝቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሐ ግብሩም የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ለበዓል መዋያ የሚኾን ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ወገኖችም በዓልን በደስታ እንዲውሉ የሚያስችላቸው መኾኑን ገልጸዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleትንሣኤ የአብሮነት ቃል ኪዳንን የምናድስበት ቅዱስ ዕለት መኾን አለበት።
Next articleቂምን በፍቅር፤ በደልን በይቅርታ በመሻር ለሀገራችን ልማት፤ ሰላምና አንድነት በጋራ መቆም ይኖርብናል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ