
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የትንሣኤ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የጉባኤው ተወካይ ቦርድ ሠብሣቢ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መላዕከ ብርሃን ፍሰሐ ጥላሁን ናቸው።
ትንሣኤ ላለፈው ጨለማ እጅ አለመስጠትን እና ለተሰበረ ተስፋ አዲስ ሕይወት መስጠት ማለት ነው ብለዋል በመግለጫቸው። በዕለቱ የሚበራው የትንሣኤ ሻማም የክርስቶስ የሞት ድል የሚበሰርበት ብርሃን እንደኾነም ገልጸዋል።
ብርሃኑም በውስጣችን ያለውን የጥላቻ፣ የቂም እና የልዩነት ጨለማ እንድናሸንፍ የሚያሳስብ መኾኑንም ነው በመግለጫቸው ያነሱት።
የኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል ሲከበር ሞት ተሸንፎ ሕይወት የነገሠበትን ታላቅ ምስጢር በማሰብ ሊኾን ይገባል ብለዋል መላዕከ ብርሃን ፍስሐ ጥላሁን።
ትንሣኤው የታወጀው ሰላም ለእናንተ ይሁን በሚል የሰላም የምስራች እንደኾነ ነው የገለጹት።
በታላቁ የትንሣኤ በዓል ምዕመኑ ልብን ለይቅርታ፣ እጅን ለእርቅ፣ መንፈስን ደግሞ ለአንድነት ክፍት ማድረግ አለበት ብለዋል። የጥል ግድግዳዎች ፈርሰው የፍቅር ድልድዮች የሚገነቡበት ጊዜም አሁን እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ክልል ያለፍንባቸው ፈተናዎች እንደ መቃበር ድንጋይ ከብደው ቢታዩም ትንሣኤ ግን ድንጋዩ እንደሚንከባለል እና ብርሃን እንደሚወጣ ያስገነዘበ ነው ብለዋል።
የትንሣኤ በዓል የሥጋ ዘመድ እና ወዳጅ የሚገናኝበት ምድራዊ አጋጣሚ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያዊያን በኅብረት ኾነን የፍቅር እና “የአብሮነት ቃል ኪዳን የምናድስበት ቅዱስ ዕለት መኾኑን ነው” የተናገሩት።
ብርሃነ ትንሣኤው ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምን፣ ለወገናችን እውነተኛ ፍቅርን እና ለልባችን ደግሞ መለኮታዊ እረፍትን እንዲሰጥም ጉባኤው መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
