ዲያቢሎስ ታሰረ !

24

 

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ታላላቅ እና ረቂቅ ምስጢራት ከሚነገሩባቸው ዕለታት መካከል የሕማማት ሳምንት ማሳረጊያ የኾነችው ቀዳም ሥዑር አንዷ ናት።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ የአራቱ ጉባኤያት መጻሕፍት ምስክር መምህር ሊቀ ሊቃውንት ሳሙኤል አሥናቀ ቀዳም ሥዑር በሐዘን እና በደስታ፤ በተስፋ እና በጉጉት መካከል የምትገኝ የሰው ልጅ የዘመናት ናፍቆት ፍጻሜ ያገኘባት ድንቅ ዕለት ናት ብለዋል።

በዚህ መጠን ለመከበሯ አንዱ ምክንያት በዕለተ ዓርብ የተከናወነው ምስጢር ተቀባይ በመኾኗ እንደኾነም ገልጸዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅሎ የሠራውን የቤዛነት ሥራ በዕለተ ቀዳሚትም በከርሠ መቃብር ቀጥሎ ነበር ነው ያሉት።

ይህችም ከዕለተ ስቅለት ቀጥላ ከታላቁ የትንሣኤ በዓል አስቀድማ ያለችው ዕለተ ቀዳም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ቀዳም ሥዑር ተብላ እንደምትጠራ ገልጸውልናል።

ሥዑር ማለት የተሻረች ማለት ነው ብለዋል። ለዚህም ሦስት ዐበይት ምስጢራዊ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል።

​👉 አንደኛው ሞት እና መቃብር የተሻረባት በመኾኗ​ ነው ብለዋል።

​👉 ሁለተኛው በጾም የምትሻር ቅዳሜ በመኾኗ እንደኾነ ገልጸዋል። በሕገ መጻሕፍት እንደተጻፈው ቀዳሚት እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ያረፈባት ዕለት በመኾኗ ጾም እንዳይጾምባት ሥርዓት ተሠርቷል ነው ያሉት።

ይኹን እንጂ በዓመት አንዲት ቅዳሜ ግን ሰማይን እና ምድርን የፈጠረ ጌታ በከርሠ መቃብር ስላደረባት ያንን በማሰብ ትጾማለች ብለዋል።

​👉 ሌላው ምክንያት ከልምላሜ ጋር የተገናኘ አስተምህሮ መኾኑን ነግረውናል። ኖኅ ከመርከብ ለመውጣት የጥፋት ውኃ መድረቁን ያወቀው ርግብ ይዛለት በመጣችው የለመለመች የወይራ ቅጠል እንደነበር ገልጸዋል።

እንደዚሁም ሁሉ በዚህች ዕለት የኃጥያት እና የመርገም ዝናብ በክርስቶስ ሞት መቆሙ፤ የዲያብሎስ ጥበብ እና የሞት ኃይል መወገዱን ለመግለጽ ካህናት “በመስቀሉ ሰላምን አወጀ” እያሉ ቄጤማ ያድላሉ ብለዋል።

ቀዳም ሥዑር በምዕመናን ልብ ውስጥ በሁለት ታላላቅ ስሜቶች የምትታሰብ እንደኾነችም ነግረውናል።

በአንድ በኩል ኃጥያት የሌለበት የባሕርይ አምላክ ስለ ሰው ልጅ በከርሠ መቃብር ማደሩን እያስታወሰ በሐዘን እንደሚያስባት ገልጸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅ ፍቅር እና የመቃብርን ኃይል ማድከሙን በማስተዋል በተስፋ ትታሰባለች ነው ያሉት።​

እነማርያም መግደላዊት ሌሊቱ አልነጋ ብሏቸው፣ ሴትነታቸው ሳይገድባቸው እና ጨለማው ሳይበግራቸው ወደ መቃብሩ በመመላለስ ትንሣኤውን በመናፈቅ ማሳለፋቸውንም ገልጸውልናል።​

ሐዋርያት “ሁሉን ትተን ተከተልንህ” ያሉትን አምላክ ትንሣኤውን በናፍቆት እንደጠበቁ የሰው ልጆችም በጾም፣ በጸሎት፣ በትሕትና እና በፍቅር ዕለተ ቀዳሚትን ከክርስቶስ ትንሣኤ እስክታደርሳቸው ድረስ በመጓጓት ያሳልፏታል ብለዋል።

ይህች ዕለት የዓለም ግርግር እና የሥጋ ዝግጅት የሚደረግባት ሳትኾን ሙሽራው ክርስቶስን ከከርሠ መቃብር በክብር ሲነሣ ለመቀበል በመንፈሳዊ መጓጓት የምትጠበቅ ቅድስት ዕለት መኾኗንም አንስተዋል።

በዓሉም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ የተነሳበት ብቻ ሳይኾን ሰላም እና ፍቅር ለዓለም የታወጀበት በዓል በመኾኑ የሰው ልጆች በዓሉን ሲያስቡ በክርስቶስ ደም የተመሠረተውን ሰላም፣ ፍቅር እና ትሕትና በልብ በማንገሥ እና ያለው ለሌለው በማካፈል ሊያከብር እንደሚገባ አባታዊ ምክራቸውን ተናግረዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤውን ለሐዋርያት ሲገልጥ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” እንዳላቸው እኛም በዚች ዕለት የሰላምን ድምጽ ለሁሉ ማሰማት ይገባናል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክርስቶስ ደም የተገዛውን የሰው ልጅ ክብር ማዋረድ አይገባም” ብጹዕ አቡነ አብርሐም
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአፍሪኤግዚም ባንክ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ኢሎምቢን ( ዶ.ር) ጋር ተወያዩ።