“በክርስቶስ ደም የተገዛውን የሰው ልጅ ክብር ማዋረድ አይገባም” ብጹዕ አቡነ አብርሐም

10

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስቅለት በዓል በባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ተከብሯል።

የባሕር ዳር እና የሰሜን ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ አብርሐም በዕለቱ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከመከራ ለማውጣት ግርፋት እና ስቃይን መቀበሉን ገልጸዋል።

ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተው ሞት እውነተኛ ነጻነት መገኘቱንም በአስተምህሯቸው አንስተዋል። በዓሉ ክርስቶስ ስለ እኛ የከፈለውን ዋጋ የምናስብበት ብቻ ሳይኾን በሕይወታችን በማንም ላይ በደል እና ግፍ እንዳናደርግ ራሳችንን የምንመረምርበት መኾን እንዳለበትም ተናግረዋል።

በሐሰት ምስክርነት ንጹሐን ሰዎችን አሳልፎ የመስጠት እና በገንዘብ የመለወጥ ድርጊት አሳሳቢ መኾኑንም ጠቁመዋል። ይህ ድርጊት በክርስቶስ ደም የተገዛውን የሰው ልጅ ክብር የሚያዋርድ መኾኑን እና ይህ ድርጊት እንደማይገባም ነው የገለጹት።

አማኞች እርስ በእርስ ከመጠላላት እንዲርቁ እና ቀደም ሲል ለፈጸሙት በደል ይቅርታ በመጠየቅ ራሳቸውን ለትንሣኤ በዓል እንዲያዘጋጁም መክረዋል።

ምዕመናን ያላቸውን በማካፈል እና የተቸገሩትን በመርዳት የበዓሉን ፍቅር እና ሰላም እንዲያሳዩም ብጹዕነታቸው መልእክት አስተላልፈዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleመሪን በንቃት መምረጥ ሥልጡንነት ነው።