
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት የገዳማት መምሪያ ኀላፊ እና የደባርቅ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የአራቱ ጉባዔያት መምህር አባ ተክለ ሃይማኖት ኃይለ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን መርገመ ስጋ፤ መርገመ ነብስን ለመደምሰስ፤ የዲያቢሎስን አገዛዝ ለመሻር እና ነብሳትን ከሲኦል ለማውጣት ወደ ምድር ወርዷል ይላሉ።
ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል መገረፉን፤ በችንካር መመታቱን፤ በመስቀል ላይ መዋሉን እና መከራን መቀበሉን ገልጸዋል።
ኢየሱስ በምድር ቆይታው ለእናቱ እየታዘዘ፤ ሙታንን እያስነሳ፤ ድውያንን እየፈወሰ እና ሌሎች ምስጢራትን እየፈጸመ መቆየቱንም ተናግረዋል።
ድውያንን በነጻ መፈወሱ ያስቀናቸው የአይሁድ ካሕናት በሐሰት በመወንጀል በመስቀል ላይ እንዲሰቀል አድርገዋል ነው ያሉት።
ኢየሱስ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ምን አይነት ተዓምራት ታዩ?
👉 የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከሁለት ተከፍሏል።
👉 መቃብራት ተከፍተው ሙታን ተነስተዋል።
👉 አለቶች ተሰነጣጥቀዋል።
👉 ፀሐይ ጨልማለች፤ ጨረቃ ደም ለብሳ ብርሃኗን ከልክላለች፤ ክዋክብት ረግፈዋል።
👉 ነብሳት ከሲኦል ወጥተዋል።
መርገመ ስጋ፤ መርገመ ነብስን በመስቀል ላይ ደምስሷል፤ በደሙ የሰው ልጆችን ነጻ አድርጓል ነው ያሉት። መስቀሉ ከወንጀለኞች መስቀያ ወጥቶ የኃይል ምልክታችን፤ የመዳኛ መንገዳችን ኾኗል ብለዋል። ስለ ሰው ልጆች ሲል የማይሞተው ሞተ ነው ያሉት።
ለሰቀሉት ጠላቶቹ ይቅርታን አድርጎላቸዋልና ይቅርባይነትን ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር፤ የበደሉንን ይቅር ማለት እና በተግባር መግለጥ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ሕይወትን ለሰዎች አሳልፎ መስጠትን፤ የተቸገሩ መርዳትን፤ የታመሙ መጠየቅን፤ ሰውን ለማዳን መከራ መቀበልን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
አይሁድ ክርስቶስን ያለ ወንጀሉ ሰቅለውታልና ሰውን ያለ ወንጀሉ አለመክሰስ፤ ከቀማኞች ጋር አለመተባበር፤ እውነትን አጣርቶ መቀበል እና የሐሰት ወንጀልን መከላከልን መማር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ፍቅር ሲል ከሰማየ ሰማያት
ወርዶ በመስቀል ላይ መሰቀሉን በማሰብ ፍቅርን፣ አንድነትን እና አብሮነትን በሕይወት ውስጥ ማስቀደም ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
