
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሄሮዶስ እንዳይገድልባት ሽሽት በበረሃ የተንከራተተችለት፤ ጥም እና ርሃቡን የታገሰችበት፤ እሾህ እና አሜካላውን ያቻለችለት፣ ከአራዊት ጋር የታገለችበት ልጇ እና ወዳጇን በመስቀል ላይ ሲሰቅሉት አንጀቷ እየተላወሰ አዘነች፤ እንባዋ እንደ ምንጭ ውኃ እየፈሰሰ አብዝታ አለቀሰች።
አይታ የማትጠግበውን፤ ልጄ ወዳጄ ኾይ እያለች የምትጠራውን፤ አብዝታ የምትወደውን፤ ደስታዋ የኾነውን አንድያ ልጇን ሲሰቅሉት መሪር እንባን አነባች፤ ጥልቁን ሀዘን አዘነች።
እንኳን ዘጠኝ ወር ላረገዘችው፤ እንኳን በጀርባዋ ላዘለችው፤ ከጡቶቿ ወተትን ላጠጣችው ልጇ ይቅርና ለፍጥረታት ሁሉ ማዘን የማይገዳት ንጽሒት እመቤት አብዝታ አለቀሰች፤ በመስቀል ላይ እያየችው አንጀቷ ተላወሰች።
በደልን ይቅር የሚለውን እንደበደለኛ ሲሰቅሉት አይታለች እና አለቀሰች፤ ወንጀለኛን በምሕረት የሚመረውን እንደ ወንጀለኛ በጦር ሲወጉት አብዝታ አዘነች። ዓለምን በመዳፉ የያዛት ልጇ በፈቃዱ ሲዋጋ፣ ሲቸነከር ተመልክታለች እና መጠን የሌለው እንባን አፈሰሰች፤ እኒያ የፀሐይ ብርሃን በማይተካከላቸው ዓይኖቿ፤ በነጹት እና እጅግ በአማሩት ጉንጮቿ እንባ አረሰረሳቸው።
ከመስቀሉ ግርጌ ኾና መሪር ሀዘንን አዘነች፤ ልጄ ወዳጄ ኾይ ሰቀሉህን እያለች በርህርሂት አንጀቷ ተንሰፈሰፈች።
ላሐ ማርያም ወሰቆቃዎ ድንግል በተሰኘው መጽሐፍ ወዳጄቼ ኾይ ይህቺ ንጽሒት ቅድስት እመቤታችን ድንግል ማርያም በድንግልና ጸንሳ ስለወለደችው የተወደደ ልጇ ጌታችን እና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን አታለቅስ? ታለቅሳለች እንጂ ተብሎ ተጽፏል።
ማርያም እንዲህ እያለች አለቀሰች፤ እንዲህም እያለች አብዝታ አዘነች ልጄ ሆይ ከመሪር ሥቃይህ የተነሳ የደረሰብኝን የብቸኝነቴን ኀዘን ከእኔ አስወግድልኝ። ወዳጄ ሆይ ተወልደህ በናዝሬት ሳሳድግህ ደስ የተሰኘሁበትም ደስታዬን ከእኔ አታርቅ።
ወዳጄ ሆይ እኔማ በልቤም እንግዲህ በዓላችንን እናከብር ዘንድ ፋሲካ ደርሷልና ወደ ሀገራችን እንመለሳለን እያልሁ በየዕለቱ ደስ ብሎኝ ነበር።
ልጄ ወዳጄ ሆይ ነገር ግን ፋሲካዬ በለቅሶ እና በኀዘን ተለወጠ። በዓሌም ወደ ዋይታ፤ ደስታዬም ወደ ልብ ኀዘን ተመለሰ እያለች አለቀሰች።
ድንግል ማርያም ልጇን አይሁድ በያዙት ጊዜ አብረዋት ይሄዱ ዘንድ ስለ ደቀመዛሙርቱ ጠየቀች፤ እነርሱ ግን አይሁዳውያንን በመፍራት ሸሽተው ነበር። በዚያ ጊዜ አብዝታ አዘነች። ልጄ ወዳጄ ሆይ ስለ ልጇ የእናት ኀዘን የከበደ ነው። የወዳጅም ሀዘን በወዳጅ ሀዘን የጸና ነው። ወዳጄ ልጄ ሆይ ከሁላቸው እስራኤላውያን ሀዘን ይልቅ የኔ ሀዘን ይበልጣል እያለች አነባች።
በድንግልና ስለ ጸነሰችው፣ በደንግልና ስለወለደችው ልጇ ታለቅሳለች እንጂ ለምን አታላቅስ? በዕለተ አርብ በጌታ ስቅለት ከእርሷ የበለጠ የሚያዝንስ ማን ሊኖር ይችላል? ከእርሷ በላይስ ማን እንባውን ያፈስሳል?
ልጄ ሆይ እነሆ ሠላሣ ዓመታትን ደስ ስታሰኘኝ ኖርህ እንጂ ከዓይኔ ዕይታ ለአንዲት ዕለት እንኳን አልተለየውህም። ዛሬ ግን ወደ እኔ መሪር ሀዘን ደረሰብኝ እያለች አዘነች።
በመስቀል ላይ ባየችው ጊዜ ሀዘኗ እጥፍ ድርብ ኾነ። በመስቀሉ ግርጌ ኾና አብዝታ አዘነች። ልጄ ኾይ በራስህ ላይ የአደረጉት የእሾህ አክሊል በራሴ ላይ ተደርጎ በአንተ ፈንታ መከራ መከራውን ሁሉ በትዕግሥት እቀበል ዘንድ በወደድሁ አለች።
ልጄ ሆይ አይሁድ አንተን በሰቀሉበት መስቀል ላይ ሳለህ በፍቅር ኀዘን እሰናበትሃለሁ። አይሁድ እየዘበቱ ምራቃቸውን የተፉበት የብርሃን መገኛ የኾነ ፊትህን በፍቅር እሰናበትሃለሁ። ልጄ ሆይ በጠሉህ አይሁድ እጅ ስለአለ ክቡር ልብስህንም በፍቅር እያሰብሁ እሰናበትሃለሁ።
ልጄ ኾይ በራስህ ስለደፉብህ የእሾህ አክሊል እያዘንሁ እሰናበትሃለሁ። ልጄ ሆይ ርቃንህን አይቻለሁና ለእኔስ ወዮ አለች።
ጌታም በዕፀ መስቀሉ ላይ ሳለ በፈቃዱ ነፍሱን አሳልፎ በሰጠ ጊዜ በምድር ከኾነው መነዋወጥ እና በሰማይም ከታዩ ተዓምራት እና መንክራት የተነሳ ዓለም በመላዋ ተናወጠች። ጨለማም ለበሰች፤ ጌታዋ ተሰቅሏል እና በንውጽውጽታ ተመታች፤ ተጨነቀች።
ወዳጄ ሆይ በአንተ ላይ ለፈጸሙት ሁሉ ወዮ እላለሁ። ልጄ ወዳጄ ሆይ እንግዲህ ሰዎችን እንደ አንተ የሚፈውሳቸውን ዐይኔ አታይምና በሽተኖቻቸውን የፈውስህ ደዌያቸውንም ሁሉ የአዳንህ አስረው ስለገረፉህ የእኔ የእናትህ አንጀት በሀዘን ተቃጠለ እያለች አዘነች አነባች።
በኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት እንኳን ምድራውያን፣ ሰማያውያን መላዕክት ደንግጠዋል፤ አዝነዋልም። የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም ሀዘን ግን ከሁሉ የላቀ ነው። ስለ ምን ቢሉ እናት ናትና።
የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት በታሰበ ጊዜ ለሰው ልጆች የከፈለው መከራ ይታሰባል። የድንግል ማርያም ሀዘንም ይታሰባል። የእርሱ መከራ ረቀቂ፣ የእርሷም ሀዘን ጥልቅ ነው።
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
