
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ እንስሳትን እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች አቅርቦትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ኀላፊ ጋሻው ሙጨ (ዶ.ር) በክልሉ በሁሉም አካባቢ ያሉትን ፀጋዎች በመለየት የእንስሳት ሃብትን በማልማት አቅርቦት እና ፍላጎትን ለማጣጣም ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ዘላቂነቱን ለማስቀጠልም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ተሠርቷል ነው ያሉት። የእንስሳት ሀብት ልማት ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ ቢኾንም በተለይ በበዓሉ የዕርድ እንስሳት እጥረት እንዳይገጥም እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን ነው የተናገሩት።
በበዓሉ የእንስሳት ሀብት ምርት እና የነዳጅ የቁጠባ አሠራርን ሰበብ በማድረግ ማኅበረሰቡ ያልተገባ ግብይት እንዳይፈጸም ታልሞ መሠራቱን ተናግረዋል። ይህም ከሌላው ጊዜ በተለየ ለበዓል መፍትሄ ለማበጀት እና ማኅበረሰቡን ካልተገባ ወጭ ለመታደግ ማስቻሉን አብራርተዋል።
በተለይም በወተት ሀብት ልማት ማኅበረሰቡን በማኅበራት በማደራጀት፣ በግለሰብ እና በአርሶ አደሮች ደረጃ ምርቱ እንዲመረት መደረጉን የገለጹት ኀላፊው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተደራሽ በማድረግ ምርቱ ወደ ገበያ እንዲቀርብ ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም የወተት ተዋጽኦ እጥረት እንደሌለ ተናግረዋል። ከአሁን በፊት በከተሞች አካባቢ የሚስተዋለውን የእንስሳት ሀብት እጥረት ለመፍታት ማኅበረሰቡ በእንስሳት ማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በወተት ልማት፣ በንብ ማነብ እና በዓሳ ሀብት ልማት እንዲሰማሩ በማድረግ ምርቱ በስፋት እንዲመረት እንደተደረገም አስረድተዋል።
ይህም ከገጠር ወደ ከተማ ይጓጓዝ የነበረውን የእንስሳት ሀብት አሁን ላይ ከተሞች እራሳቸውን ወደ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ የተረጋጋ ግብይት እንዲከውን እና በዓል እንዲያሳልፍ የተሻለ ሥራ በቅንጅት መሠራቱን ነው ያስረዱት። ከዚያ ባለፈም በየአካባቢው ያሉ ምርቶች በመጠን፣ በጥራት እና በዓይነት ተለይተው ለማኅበረሰቡ መረጃዎችን በመስጠት ተጠቃሚ ለማድረግ መሠራቱን አስረድተዋል።
በዘርፉ የተሰማሩ ባለ ሀብቶችን፣ ወጣቶችን እና ሌሎችንም ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለማዕከላዊ ገበያ የማቅረብ ሥራ ተሠርቷል። ከወተት ሀብት አንፃር በቀን ከ240ሺህ በላይ ሊትር ወተት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ይቀርባል ብለዋል። የዕርድ እንስሳት ጭርም እየቀረበ መኾኑንም ተናግረዋል።
የእንስሳት ሀብቱን ማልማት የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባለፈ ለሥርዓተ ምግብ እና ለኢኮኖሚ ዕድገት ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በቀጣይ በጥራት፣ በዓይነት እና በመጠን የእንስሳት ሀብት ልማቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እንደሚሠራም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
