
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስቅለት በዓል በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከኃጥያት ለማዳን ሲል መከራ የተቀበለበት፤ ራሱን አሳልፎ የሰጠበት፤ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር በመስዋዕትነት የገለጠበት በዓል ነው።
ምዕመናን ዕለቱን በጾም፣ በጸሎት እና በስግደት የክርስቶስን መከራ እና ሞት እያስታወሱ በታላቅ በተማጽኖ እና በሃዘን ያሳልፉታል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ዕለቱ ከጠዋት እስከ ምሽት በሰዓታት በተከፋፈለ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ክዋኔዎችም ይከበራል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የመንበረ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ስብከተ ወንጌል ኀላፊ መጋቢ ሐዲስ ስማ ኮነ ያየህራድ በዕለቱ ስለሚከናወኑት ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ለአሚኮ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ተዓምረ ማርያም፣ ተዓምረ ኢየሱስ፣ የዕለቱ ስንክሳርም ይነበባሉ። የዕለቱ ወንጌልም ከወትሮው በተለየ መልኩ በዜማ ይነበባል። በኋላም ኪራያላይሶን እየተባለ ይጸለያል ነው ያሉት።
በዚህ ሰዓት ለሰዓቱ የተያዙት የዳዊት መዝሙራት፣ የውዳሴ ማርያም፣ የነበያት፣ የመሐለዬ ጸሎት እና የወንጌል ምንባባት ይነበባሉ።
ምሥለ መሥቀሉ ከመቅደሱ ፊት ለፊት ይወጣል። ሁለት ከበሮዎች ጥቁር መጎናጸፊያ ለብሰው በግራ እና በቀኝ በማስቀመጥ ክዋኔው ይከወናል ብለዋል። ጌታን ያንገላቱበትን ድርጊት በሚያስታውስ መንገድ ሥርዓቱ ይከወናል፤ ስግደት ይሰገዳል ነው ያሉት።
ይህንን በማስታወስም በዕለተ ሰዓቱ የተመደቡት የጸሎት ምንባባት ይነበባሉ። ክርስቶስን መራራ ሀሞት እንዳጠጡት ለማጠየቅ ከጽናው ላይ
ከርቤ ይደረጋል። “ለመስቀልከ እንስገድ” እየተባለ ስግደት ይከናወናል ብለዋል።
የስግደት ሥነ ሥርዓቱ በዕዝል የዜማ ስልት እየተመራ”ኪሪያላይሶን” እየተባለ ይሰገዳል። “አቤቱ ጌታ ኾይ በመንግሥትህ አስበን” እየተባለ 36 ጌዜ እንደሚጸለይ ገልጸውልናል።
ሙሉው መዝሙረ ዳዊት፣ አንቀጸ ብርሃን፣ የነቢያት እና የውዳሴ ማርያም እና ሌሎችም ምንባባት ይጸለያሉ፤ 400 እግዚኦታ ይደረሳል ነው ያሉት።
በዚህ ሰዓት ስግደት አይሰገድም። ንሴብሖ የሚለው መዝሙር ይዘመራል ብለዋል።
ምእመናን በጾም እና በጸሎት በቆዩበት በሕማማት ሳምንት የሠሩትን ኃጥያት በመናዘዝ የሚሰጣቸውን ንስሐ የሚቀበሉበት ሥርዓት እንደኾነ ነው የነገሩን።
በመጨረሻም “በሰላም ግቡ” ተብሎ ምዕመናን ወደ ቤታቸው ይሰናበታሉ።
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል አደረሳችሁ።
በአሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
