
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሚገኙ ተገልጋዮች ቀናትንና ወራትን ይፈጅባቸው የነበረውን የተቋማት አገልግሎት በደቂቃዎች ውስጥ ማግኘት ጀምረዋል። ይህ የተሳለጠ አሠራር እውን ሊሆን የቻለው “ሞሶብ” የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ነው።
ቴክኖሎጂና ምቹ የሥራ ከባቢ
የአማራ ክልል ሥራና ክሕሎት ቢሮ ባለሙያው ሰለሞን ገበየሁ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በመደገፉ ደንበኞች ጉዳያቸውን በደቂቃዎች ውስጥ እንዲጨርሱ አስችሏል። ይህም ቀደም ሲል የነበረውን እንግልትና የቢሮክራሲ ሰንሰለት ሰብሮታል።
የንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ባለሙያዋ ሀሲና ማሩፍ ለማዕከሉ የተፈጠረው ምቹና ዘመናዊ የሥራ ቦታ ለሠራተኛውም ሆነ ለተገልጋዩ ከፍተኛ መነቃቃትን መፍጠሩን ገልጻለች። “ሞሶብ በአገልግሎትም ሆነ በሥራ ከባቢ አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል” ስትልም ምስክርነቷን ሰጥታለች።
“ሞሶብ” በቁጥር
የአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሥተባባሪ ተማረ አቤ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ሥራ ከጀመረበት ከባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ውጤቶችን አስመዝግቧል፦
”በማዕከሉ ተገልጋይ፣ አገልግሎት እና አገልጋይ ተነጣጥለው አይታዩም፤ ሁሉም ተቀናጅተው ፈጣን ውጤት እንዲመጣ ተደርጓል” ነው ያሉት አቶ ተማረ አቤ።
የደንበኞች ምስክርነት
በማዕከሉ ጉዳያቸውን ያስፈጸሙ ደንበኞች እንደሚናገሩት፣ መሶብ ጉዳይ ከማስፈጸም ባለፈ በቴክኖሎጂ የታገዘና ውብ ከሆነው የሥራ ቦታ ትልቅ ትምህርት ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል። ግፊያ፣ ጥድፊያና ድካም የቀረበት ይህ አሠራር ለሌሎች ተቋማትም አርአያ የሆነ ነው ብለዋል። ቀናትንና ወራትን ይወስዱ የነበሩ አገልግሎቶችን ከ20 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ማስፈፀም መቻላቸውን ተናግረዋል።
የወደፊት ዕቅድ
ማዕከሉ አሁን ከሚሰጣቸው 61 አገልግሎቶች በተጨማሪ፣ በቅርቡ ሌሎች በርካታ ተቋማትን ወደ ማዕከሉ በማስገባት አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።
አገልግሎት ሰጪዎቹም በሙያቸው ተመዝነው ያለፉና በሥነ-ምግባራቸው የተመሰከረላቸው መሆናቸው ለማዕከሉ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በሞሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተስተናግደው ያውቃሉ? አስተያየተዎን ያጋሩን።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
