
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሚሻ ሚሾ የሰው ልጅ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከባርነት ወደ ነፃነት የተሻገረበት ቃል ኪዳን የሚታሰብበት ውብ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው። በማለዳ ጀንበር በእለተ ስቅለቱ በልጆች ውብ ዜማ እና በሌሎች ሥርዓቶች ይታጀባል።
በኢትዮጵያ ኦሮርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የምሥራቅ ጸሐይ ጉባኤ ቤት የአራቱ ጉባኤያት ትምህርት ቤት የትርጓሜ መምህር ዘመላክ ዳግም ሚሻሚሾ ሆ ምሸ ምሸ ወይም ደግሞ መሸ መሸ ማለት እንደኾነ ነግረውናል።
ታሪካዊ ሃይማኖታዊ ዳራ እና ትውፊቱ ከቤተ አይሁድ የመጣ ነው ብለዋል። ሕጻናት እና ወጣቶች በእሳት የተለበለበ በትር ይዘው እየዞሩ ሆ ምሻ ምሸ ወይም አሚሻ አሚሾ እያሉ እያዜሙ በየሠፈሩ ዱቄት እና ለእለት ምግብ የሚኾኑ ነገሮችን ይቀበላሉ ነው ያሉት። ዘገር በትር መያዛቸው የዘገር ጦር ምሳሌ ነው ብለዋል።
አይሁዶች ሁለት ጊዜ አዋጅ እንዳወጁም ተናግረዋል። መጀመሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊሰቀል ሐሙስ ምሽት ክርስቶስን ለመያዝ በየ ቤቱ እየቆፈቆፉ ” እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” እያለ የሚጣራውን የዮሴፍን ልጅ ልንይዝ ነውና ውጡ እያሉ ሕዝቡን ቀስቅሰውት ነበር ነው ያሉት።
ሁለተኛው ደግሞ ምሾ ምሾ ወይም ደግሞ መሸ መሸ ውጡ ክርስቶስን የምንይዝበት ደርሷል ያሉበት መኾኑን ገልጸዋል።
ከዛም በአዋጁ መሠረት አርብ ምሽት ክርስቶስን በመያዝ፣ ክርስቶስን በመግረፍ፣እና በመስቀል ያልተባበረ ቤቱ ይቃጠላል፣ ሀብቱ ይዘረፋል ተብሎ የተነገረውን ለመተግበር በየቤቱ ዞሩ። ከዛም ዘገር ጦር በየ እጃቸው ይዘው ያልተባበራቸውን ውሾ ውሾ በማለት ቤቱን ያቃጥሉ፣ ንብረቱን ይዘርፍ፣ ይገርፋ ነበርና የዛ ምሳሌ ተደርጎ ይታሰባል ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስን መከራ ለማሰብ ሕጻናቱ በዜማ በዓሉን ያጅቡታል ነው ያሉት።
የተዥጎረጎረ ጫፉ የሾለ በትር የሚይዙትም ከዚህ ጋር የተሳሰረ መኾኑን ገልጸዋል። በዓሉ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው እንጂ በዘልማድ የመጣ አለመኾኑን አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
