ከጫካ ወደ ሰላም፤ ከጥፋት ወደ ልማት!

32

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቀደም ሲል ሲከተሉት የቆዩት የጥፋት መንገድ አገርንና ሕዝብን የሚጎዳና የታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት ለማሳካት ያለመ በመሆኑ የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን ራሱን አፋብን ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን የቀድሞ አመራር አባላት ገለጹ።

በጥፋት ቡድኑ ተታለው ጫካ የገቡ ወንድሞቻቸውም ወደ ሠላም አማራጭ እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።

እጃቸውን በሠላም ለመንግስት የሰጡ የጽንፈኛ ቡድኑ የቀድሞ አመራር አባላት እንደገለጹት፤ እስከአሁን ሲከተሉት የቆዩት መንገድ ለክልሉ ሕዝብ አንዳች ጥቅም እንደሌለው በመረዳታቸው የሰላም አማራጭን ተቀብለዋል።

በጫካ ቆይታቸው የተረዱት እውነታ “ለሕዝብ እንታገላለን” በሚል መፈክር ሽፋን የቀድሞ ሕወሃትና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችን ፍላጎት ለማሳካት የተጠለፈ ትግል መሆኑንና ሕዝብን ለጥፋት ለመዳረግ ያለመ አካሄድ መሆኑን ተገንዝበዋል።

እጃቸውን በሰላም ከሰጡት ራሱን አፋብን ብሎ ከሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን አመራሮች መካከል የቀድሞ የኮር ፖሊት መምሪያ ኃላፊ ጌራወርቅ ዳኛው፤ የአማራ ሕዝብ ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚረጋገጠው በሰላማዊ መንገድ መታገል ብቻ በመሆኑ ሰላማዊ አማራጭን ለመከተል ወስኛለሁ ብሏል።

የጽንፈኛ ቡድኑ አመራሮች ከክልሉም ሆነ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የልማት ፍላጎት በተጻራሪ በመቆም ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተባብረው ጥፋት በማድረስ ላይ ናቸው ያለው ጌራወርቅ፤ በማኅበራዊ እሴቶችና መሰረተ ልማቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ጥቃት ከጀርባው የጥፋት ሴራ እንዳለው አመላካች መሆኑን ተናግሯል።

ራሱን አፋብን ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን የቀድሞ አመራር አባል ሀምሳ አለቃ ፍቅሩ ሙልዬ በበኩሉ፤ የጽንፈኛው ቡድን አመራሮች ከሕዝብ ፍላጎት ይልቅ ለኢትዮጵያ ጠላቶችና ለግል ጥቅማቸው እየሰሩ መሆኑን ጠቁሟል።

ለጽንፈኛው ቡድን የተለያዩ ጥያቄዎች ሲነሱ የትግል አጋርን በመፈረጅ የማሸማቀቅና አልፎም ሰበብ ፈልጎ የማስወገድ ተግባር እንደሚፈጸም አስረድቷል።

እነርሱ ልጆቻቸውን ውጭ ልከው እያስተማሩ የደሃ ልጆችን ግን ለመስዋዕትነት እየዳረጉ ነው ሲል ሀምሳ አለቃ ፍቅሩ አብራርቷል።

ሌላው የቡድኑ የቀድሞ አመራር አባል እና ኮር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር አየነው አስፋው እንደገለጸው፤ ራሱን አፋብን ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድን አመራሮች ፍላጎት ትግሉን በማራዘም የራሳቸውን ሀብት ማካበት ላይ ማተኮር ነው።

ለትግል በሚል የተጀመረው ዓላማ የሕዝብን የልማትና የእድገት ፍላጎት የሚያደናቅፍ፣ አንዳች ፋይዳ የሌለው መሆኑን መረዳቱን አመልክቶ፤ ለህዝብ ጥቅም እንቆማለን የሚሉት የጥፋት ቡድኑ አመራር አባላት ቤት በመስራት፣ ተሽከርካሪ በመግዛትና ሀብት በማካበት መጠመዳቸውን ገልጿል።

በጥፋት በድኑ ራሱን የሸዋ ፋኖ ጠቅላይ ግዛት ብሎ የሚጠራው የቀድሞ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ማንነገረው መለሰ እንደገለጸው፤ የግለሰቦችን የሥልጣን ፍላጎት ለማርካት የሚደረገው እንቅስቃሴ ሀገርን ከመጉዳት የዘለለ ፋይዳ የለውም።

የቡድኑ አመራሮች ምንም ዓይነት ግልጽ ፖለቲካዊ እውቀት፣ መርህና ዝግጁነት የሌላቸው መሆኑን ጠቅሶ፤ ሕዝቡ የቡድኑን እውነተኛ ማንነት ሊገነዘብ እንደሚገባም አሳስቧል።

ይህ አካሄድ ሕዝብም የማይደግፈው ውጤት የማያመጣ መሆኑን መረዳቱን ጠቅሶ፤ ሰላማዊ አማራጨ በመቀበል ለመጓዝ መምረጡን ተናግሯል።

የመረጡት የሰላም አማራጭ የጥፋት ተልዕኮ ሳራዘም በክልሉ ሰላም ግንባታ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሆነ ማስገንዘባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በዚህም እኛ የሰላም አብሪ ሆነናል ያሉት የቀድሞው ጽንፈኛ ቡድን አመራር አባላት፤ በቀጣይም ቀሪ በጫካ የሚገኙ ወንድሞቻችን የመንግሥትን የሰላም አማራጭ በመቀበል ለአማራ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ሰላም መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንድያይሺሚዬ ጋር ተወያዩ።