በጤና ተቋማት የነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር ምን እየተሠራ ነው ?

3

 

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሚገኙ ጤና ተቋማት መካከል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጉሃላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አንዱ ነው።

የጉሃላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሥራ አሥኪያጅ ደርሶ ሲሳይ ሆስፒታሉ ከ200 ሺህ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የመብራት መቆራረጥ ችግር እየገጠመው እንደኾነም ገልጸዋል። ለዚህም ችግሩ ሲገጥም ነዳጅን ተጠቅሞ በጄኔሬተር አገልግሎት እየተሠጠ እንደኾነ ነው ያነሱት።

ሆስፒታሉ በሚገኝበት ከተማ የነዳጅ ማደያ አለመኖሩ ለሥራቸው እንቅፋት እንደኾነባቸው ተናግረዋል።ይህ ደግሞ መብራት ሲጠፋ በጄኔሬተር በሆስፒታሉ የሚሰጡ የላበራቶሪ ምርመራዎች፣ ቀዶ ጥገና አገልግሎቶች እና በሪፈር ወደ ሌሎች ተቋም ለሚላኩ ታካሚዎች የአንቡላንስ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸውም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕክምና እና ታድሶ አገልግሎት ዳይሬክተር ድንበሩ ባየልኝ አሁን ካለው የነዳጅ አጠቃቀም ሁኔታ ጋር ተያይዞ የጎላ ባይኾንም ችግሮች እንደተስተዋሉ ገልጸዋል።

ይህንን ለመቅረፍም ለጤና ተቋማቱ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጡ እየተደረገ እንደኾነ ተናግረዋል። በዚህም እስካሁን ባለው ሁኔታ የገዘፈ ችግር አለመኖሩን አንስተዋል።

ሕክምና የ24 ሰዓት አገልግሎት በመኾኑ በዚህ ሂደት የመብራት መቆራረጥ ሊገጥም ይችላል ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ጄኔሬተር አስፈላጊ በመኾኑ ነዳጅ እንደሚያስፈልግ ነው የገለጹት። ከፍ ያለ ሕክምና የሚያስፈልገው ታካሚ ሲኖር በሪፈር ወደ ሌሎች ተቋማት ለመላክ አጋዥ ለኾኑት አንቡላንሶች ነዳጅ አስፈላጊ እንደኾነም ተናግረዋል።

አሁን ላይ የተፈጠሩ ውስን ክፍተቶች እና ቀጣይ ሊገጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን ታሳቢ ያደረገ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች በትኩረት እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል።

በቀጣይ ጉሃላ እና ሌሎች በአቅራቢያቸው የነዳጅ ማደያ የሌላቸው ሆስፒታሎች ውል ወስደው ለጤና ተቋማት እና አንቡላንሶች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው የሚያደርጉ ሥራዎች ይሠራሉ ብለዋል።

በተለያየ ምክንያት ችግር ለገጠማቸው የጤና ተቋማት መፍትሔ ለመስጠትም ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጥረት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአፍሪካ ከውጭ እርዳታ እንድትላቀቅ የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅምን በገንዘብ ማጠናከር ይገባል።