
ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፤ የፋይዳ ዲጅታል መታወቂያ እና የኢትዮ ኮደርስ አፈጻጸምን ገምግመዋል።
በውይይቱ 15 ሚሊዮን ነዋሪዎች የፋይዳ መታወቂያ እንዲያወጡ እየተሠራ መኾኑም ተጠቅሷል። 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ነዋሪዎች የፋይዳ መታወቂያ አውጥተዋል ተብሏል። በክልሉ የኮደርስ ሥልጠና በስፋት እየተሰጠ መኾኑም ተጠቁሟል።
በ2018 በጀት ዓመት 38 የመሶብ ማዕከላትን አስገምብቶ ለማስመረቅ እየተሠራ መኾኑ ተነስቷል። ከ72 ሺህ በላይ አገልግሎቶችን በሦሥት ማዕከላት መሰጠቱም ተጠቁሟል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ፋይዳ መታወቂያ፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት እና የኮደርስ ተግባራት የበጎ አድራጎት ሥራዎች አይደሉም፤ የመንግሥት ልዮ ፕሮጀክቶች ናቸው ብለዋል።
ሥራዎቹ ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሠሩ በመኾናቸው ስኬታማ ለማድረግ በቁርጠኝነት መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዘርፎቹ የሴቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ፋይዳ የሁሉ ነገር መሠረት በመኾኑ ማኅበረሰቡ እንዲያወጣ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የመንግሥት ሠራተኞች የፋይዳ መታወቂያ እንዲያወጡ እና የኮደርስ ሥልጠና እንዲወስዱ በልዩ ትኩረት መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል።
የዲጅታላይዜሽን ዘመን ላልተጠቀመበት አግላይ ለተጠቀመበት ደግሞ አትራፊ ያደርጋል ነው ያሉት። ከዲጅታል ሥርዓት ወደ ኋላ መቅረት እንደማያስፈልግም ተናግረዋል።
የመሶብ አንድ አገልግሎት ማዕከላትን በፍጥነት እና በጥራት መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል። አሁን ላይ የአገልግሎት ቅልጥፍና እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት እንዲደረግም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
